በነስረዲን ኑሩ
የካቲት 13/2014 (ዋልታ) በአፍሪካ ትልቁ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ የኅዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠ 11 ዓመታት በኋላ ዛሬ የካቲት 13 ቀን 2014 የመጀመሪያ የኤሌክትሪክ ምርቱን (ኃይሉን) ‘የምስራች’ ሲል እንካችሁ ብሏል።
በአገራችን ባሕል አርሶ አደሩ ለበርካታ ዓመታት የደከመባቸው ተክሎች ትዕግስትን፣ ጉልበትን እና ምጣኔ ሃብትን በእጅጉ ከሚፈታተን ትግል በኋላ የመጀመሪያውን ምርት ሲሰጥ ‘የምስራቹን’ ሰጠ ይባላል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ጅማሮ በቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባስቀመጡት የመሰረት ድንጋይ ከተበሰረበት መጋቢት 24/2003 ዕለት አንስቶ ዛሬ ከደረሰበት እንዲደርስ በርካታ ፈተናዎችን ማለፍ ነበረበት።ከፈተናዎቹ መካከል ግብጽ መራሹ ኢ -የኅዳሴ ግድብ ዓለም ዐቀፍ ቡድን የግድቡን ግንባታ በማሰናከል የኢትዮጵያዊያንን ህልም ለማጨንገፍ የተጓዘበት ርቀት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ ዛሬም የቀጠለ ሴራ ነው።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹክሪ በተለይ የመጀመርያው ዙር የውሃ ሙሌት መከናወኑን ተከትሎ ባሉት የሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ 22 አገራት ጉዞ ማድረጋቸውን በአብነትነት ማንሳት ይቻላል።
ሳሚ ሹክሪ እነዚህን አገራት በዚህ ፍጥነት ያካለሉት በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሱ የሚገኙት የአረብ ሊግ አባል አገራቱ የመን እና ሶሪያ ጉዳይ አስጨንቋቸው መፍትሔ ለማፈላለግ አልነበረም፤ ዓለም ዐቀፍ ጫናን በመፍጠር የኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን ተስፋ ለማኮላሸት እንጂ።
በሌላም በኩል 5 ሺሕ ንጹሃንን በታህሪር አደባባይ ላይ አስጨፍጭፎ ወደ ሥልጣን በመጣው መሪዋ አብዱልፈታህ አልሲሲ በኩል ከምታስተላልፈው የዛቻና ማስፈራሪያ መልዕክት በተጨማሪ ወታደራዊ ልምምድ በሚል ሽፋን ከሱዳን ጋር አፍንጫችን ስር ስትልኮሰኮስ እንደነበር መች እንረሳውና?
የእነግብፅና አሜሪካ የጥቅም ቁርኝት ኅዳሴ ግድብን ለመስዋዕትነት ለማቅረብም ታትሯል። ለግንባታውም ይሁን ለሌሎች የልማት ሥራዎች የእርዳታና የብድር ገንዘብን ኢትዮጵያ እንዳታገኝ የዓለም ባንክና የዓለም ዐቀፉን ገንዘብ ተቋም አድራጊ ፈጣሪዎች አሳምፆም ነበር። ግና ግድቡ የጀግንነት ምልክት ነውና ግንባታው በትልቁ በውስጥ የገንዘብ አቅም ቀጥሏል።
ስለ ሴራዎቹ ስናነሳ ሌላው ቀርቶ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ከተቋቋመለት ዓላማ እና የሥራ መርህ ውጭ በኅዳሴ ግድቡ ጉዳይ ውሳኔ ሊያስተላልፍ መቀመጡ ግብጽ መራሹ ዓለም ዐቀፍ ጫናው ምን ያህል ከባድ እንደነበር ያረጋገጠ ነው።
ወትሮም ቢሆን የውጭ ጫናው ሲበረታ እና አገር ስትደፈር ፍጹም አንድ ሆኖ ጥቃትን የመመከት ልምድ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኅዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ በከፍተኛ ቁጭት እልህና ድህነትን የማሸነፍ ወኔ ተሳትፎ አድርጓል።
የኅዳሴ ግድቡ እዚህ እንዲደርስ ሴት ወንድ፣ ወጣት ሽማግሌ፣ እስላም ክርስቲያን፣ ሰሜን ደቡብ፣ ምስራቅ ምዕራብ፣ አገር ውስጥ ያለ ዲያስፖራ ሳይለይ መላው ኢትዮጵያዊ ከዚህ ቀረ የማይባል ድጋፍ አድርጓል።
በእርግጥ የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ በተቀመጠለት ጊዜ ባይጠናቀቅም ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በተወሰደው የማስተካከያ እርምጃ የግንባታው ዋና ዋና ሂደቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ሲከናወኑ ተስተውሏል።
ኢትዮጵያ አሸባሪው ትሕነግ በለኮሰው ጦርነት ውስጥ ሆናም እንኳን የውሃ ሙሌቱን በእቅዷ መሰረት ማከናወኗ የግድቡ ጉዳይ ለኢትዮጵያዊያን የሞት እና ሽረት መሆኑን ግብጽን ጨምሮ ለመላው ዓለም በድጋሚ ያረጋገጠችበት ነው።
አትዮጵያ ፈርጀ ብዙ በሆነ ጦርነት ውስጥ እንደመሆኗ የውሃ ሙሌቱ ከጦርነቱ በኋላ ይደርሳል ሳትል ማከናወኗ በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኅዳሴ ግድቡ ለአፍታም እንኳን አይናችንን ዞር የማናደርግበት ዋነኛ ጉዳያችን ነው ያሉትን አባባል በተግባር ያረጋገጠ ነው።
በእርግጥ የዛሬው ምስራች ላይ እንደተገለፀውም በኅዳሴ ግድቡ ግንባታ ውስጥ ያለፉት 3ቱም ጠቅላይ ሚኒስትሮችም ይሁኑ ሕዝቡ ወጥ አገራዊ አቋምን ይዘው የፀኑበት እውነት አደባባይ ላይ ነው። ይህም ነው መሪ አልፎ መሪ ሲተካ ሙሉ በሙሉ ከመወጋገዝ ታሪካችን በመለስ በግድቡ ጉዳይ መመሰጋገንን ደጋግመን ያስተዋልነው።
የሆነው ሆኖ እንደ ጠላቶቻችን ሴራ፣ ምኞትና እቅድ ሳይሆን ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ያቀደችውን እየከወነች በከፍታ መጓዟን ቀጥላለች።
እዚህ ላይ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት እየተከናወነ ባለበት ወቅት ግብጻዊ ተንታኝ የመሰከረውን እውነት በማስታወስ ጽሑፌን ልቋጭ።
“ለምን እንዋሻለን። ኢትዮጵያ ተናግራ ያልፈፀመች ምን አለ? ለምን እንዋሻለን ማን አለ እንደ ኢትዮጵያ የሚናገረውን የሚኖር? ማንም የለም ሲል ሐሳቡን ያስረዳል።
የአሜሪካን በማር የተለወሰ የመርዝነት አደራዳሪነት አልፈልግም አለች። አሜሪካ ተገዳ ከታዛቢነት ስፍራዋ ገሸሽ ተደረገች።
በተመሳሳይ የዓለም ባንክ በታዛቢነት ስም ወንበር ይዞ የአደራዳሪነት ሚናን የመውሰድ ፍላጎትም ከሸፈ።
የተባበሩት መንግሥታት የውሃን ጉዳይ በተመለከተ የመወሰን መብት የለውም፤ ኅዳሴ ግድብ የልማትና የውሃ እንጂ የፀጥታና ደኅንነት ስጋት ጉዳይ አይደለም በሚለው ሙግቷም መርታት ችላለች። መንግሥታቱ ተረቶም የአፍሪካ ኅብረት የአስተባባሪነቱን ሚና ይውሰድና ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔን ሳይወድ በግዱ እንዲውጠው አድርጋለች።
የመጀመሪያውን ሙሌት እሞላለሁ አለች ! ሞልታ አሳየችን።
ሁለተኛውን ሙሌት ያለ ሁለቱ አገሮች ስምምነት መሙላት አትችይም ተብላ በሱዳንና ግብፅ ቢነገራትም በ2015ቱ የመርሆዎች መሰረት ሁለተኛውን ሙሌት ከመፈፀም የሚያግደኝ ምድራዊ ሀይል የለም አለች፤ አደረገችውም።
የአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግብፅ ግድቡን በቦንብ ልታፈነዳው ትችላለች ሲሉ ቀሰቀሱ። የሆነው ግን ትራምፕም ከሥልጣናቸው ወረዱ ግብፅም አላፈነዳችው ይልቁንም የትብብር ማሳያ ከሆነው ግዙፍ ግድብ ኢትዮጵያ ዛሬ ኃይልን አመነጨችበት። ይኸው ነው!