እንደ ሀገር ከ400ሺሕ ሄክታር መሬት በላይ በበጋ መስኖ ስንዴን ለማልማት እየተሰራ ነው

ኅዳር 17/2014 (ዋልታ) በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን በ145 ሄክታር መሬት የጋሞ ልማት ማህበር እርሻ ልማት ላይ የ2014 አገራዊ የበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት ሥራ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተጀምሯል።

ለዚህም በክልል ደረጃ በበጋ መስኖ ከ15ሺሕ ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን እንደ ሀገር ከ400ሺሕ ሄክታር በላይ በበጋ መስኖ ስንዴን ለማልማት እየተሰራ እንደሆነ ተገልጿል። በዚህም 16 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱ ተጠቁሟል።

በማስጀመሪያ መርኃግብር የተገኙት በግብርና ሚኒስቴር የግብርናና ሆልቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በኅልውና ዘመቻ ላይ ባለችበት ወቅት ወደ ግንባር በመዝመትና በልማት በመትጋት የመሪያችን አደራ እንወጣለን ብለዋል፡፡

በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው እንደ ሀገር የምግብ ፍላጎትን ለማረጋገጥ የሀገርን ሀብት በዕውቀት መምራት ከብክነት ማፅዳት እና በትኩረት መምራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ብርሃኑ ዘውዴ በዞኑ ለም አፈር፣ ምቹ አየር እንዲሁም በቂ የውሃ ሀብት ያለው ዞን በመሆኑ በግብርናው ዘርፍ ለሚደረጉ ምርምሮችና ሙከራዎች የልቀት ማዕከል እየሆነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በአክሊሉ ሲራጅ