እንደ ሀገር የተጋረጠብንን አደጋ የምንመክትበት መንፈሳዊ ስንቅና ብርታት ያስፈልገናል – የሰላም ሚኒስቴር

ሐምሌ 27/2013 (ዋልታ) –  እንደ አገር የተጋረጠብንን አደጋ  የምንመክትበት  መንፈሳዊ  ስንቅ፣ ብርታት ጽናት ያስፈልገናል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አስታወቁ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 13ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ  ላይ  የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት  ካሚል  የሐይማኖት  አባቶች፣  የክልሎች ና የከተማ መስተዳድሮች የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል  የኢትዮጵያ የሐይማኖት  ጉባኤ  ምዕመናን  ችግር  ሲገጥማቸው  ከችግር የሚወጡበትን  መንፈሳዊ  ጥንካሬን  ሲሰጥ ነበር ብለዋል።

ይሕም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል ከፍተኛ አስተዋጽኦ  ማድረጉንና ባለፉት ሦስት አመታት የገጠሙንን  ችግሮች  ጸሎትንና የመንፈስ ምግብን እንደ ስንቅ  በመያዝ  አብረን  ተጉዘናል  ነው ያሉት።

ሐይማኖትና መንግሥት በጋራ በመደጋገፍ ሥራዎችን እንደሚሰሩና ጉባኤውም ይህንን አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ  እምነታቸው  መሆነን አመልክተዋል።

“ያለንበት ወቅት የሰላምና የብልጽግና ጉዞ  ለማስቀጠል  የምንሰራበት  በሌላ በኩል ለዘመናት የተከማቹ  ችግሮች  የተከሰቱበት  በመሆኑ ችግሮቹን  በመቅረፍ  የትስስር  ሰንሰለት  የምንቀጥልበትን መንገድ ለመስራት የሐይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ ነው ” ብለዋል።

የኔ ዐሳብ ብቻ  ይደመጥ  የሚል አስተሳሰብ፣ ጥላቻና መራራቅ አገር እንዳትጸና የሚያደርግ መሆኑን አመልክተው ፖለቲካው ፍቅር ሰላም መተዛዘንን  አብሮነትን  እንደሚያስፈልገው ገልጸው፤ አገርን ማጽናት የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው ሲሉ  ጠቅሰዋል።

እንደ አገር የተጋረጠብንን አደጋ የምንመክትበት የመንፈሳዊ ስንቅ ብርታት ጽናት ያስፈልጋል  ሲሉም ነው ያስታወቁቅ።

ይህንንም ለማድረግ የሐይማኖት አባቶች ሚና ሰፊ ድርሻ ያለው በመሆኑ  ፈተናውን  በጋራ  ጸንቶ  ማለፍ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አደለም ሲሉም ተናግረዋል።

በጸሎት በምሕላ ኢትዮጵያ ጸንታ የምትቆምበትን መንገድ እንድትሰሩ ያስፈልጋል በማለት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ  ሐይማኖት  ተቋማት  ጉበኤ  የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በበኩላቸው የሐይማኖት አባቶች እውነተኛ የሰላም ሐዋርያ በመሆን ልንሰራ ይገባናል ብለዋል።

የአገር ሰላም በምኞትና ፍላጎት ብቻ አይመጣም፣ ጽኑ ተከታታይና ሰፊ ስራ በመሥራት የሚገኝ ውጤት መሆኑን ልንገነዘብ ይገባናል ነው ያሉት።

ስለዚህም ሁላችንም በከፍተኛ ተነሳሽነት ልንሰራ ይገባናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።