እየተባባሰ የመጣው ግጭትና አለመግባባት የኔ ሀሳብ ብቻ ልክ ነው የሚል እሳቤ በመስፋፋቱ ነው – የሀገራዊ ምክክር ኮምሽነር ዮናስ አዳዬን

ግንቦት 16/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው ግጭትና አለመግባባቶች የኔ ሀሳብ ብቻ ልክ ነው የሚል እሳቤ እየተስፋፋ በመምጣቱ የተከሰተ መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ኮምሽነር ዮናስ አዳዬን (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ኮምሽነሩ ዜጎች በሀገራቸው ሰላምና ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዳይንቀሳቀሱ የኢትዮጵያን አንድነት የማይሹ አካላት ግጭትን በመፈብረክ በርካታ ደም መፋሰሶች እንዲከሰቱ አድርጓል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የሰላም መደፍረስ ታይቷል። ብዙዎች ከውስጥም ከውጭም ተቀናጅተው የሀገርን ሰላም ለማናጋት ተንቀሳቅሰዋል።
ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት መምህር ዮናስ አዳዬን (ዶ/ር) ከዕለት ዕለት፣ ከአመት አመት እየጎለበተ የመጣው የመከፋፈልና የመገፋፋት ስሜት ሕዝቦች በአንድ ተቀምጠው የሚመክሩበትን ተገናኝተው የሚወያዩበትን ተወያይተውና ተግባብተው የጋራ መተማመን ላይ የሚደርሱበትን መድረክ እንዳይኖር አድርጎታል ብለዋል፡፡
የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት በመጠበቁ ረገድ ትልቁን ሚና የሚወስደው መንግሥት በሀገር ላይ ሰላምን የማስከበር የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነትም ግዴታም አለበት። ይሄንን ኃላፊነቱን በሚገባ ሊወጣ ይገባልም ሲሉ ገልፀዋል።
የሕዝቦች መገናኛ እና መወያያ መድረክ በጠፋ ቁጥር የልዩነት አራጋቢዎች፣ የግጭት አባባሾች፣ የኹከት ድግስ ጠማቂዎች መድረኩን እየተቆጣጠሩ የሕዝቡን ተነጋግሮ በመግባባት የጋራ የሚለው የወል እሴቱን እንዳያሳድግ ይልቁንም አፍ ለአፍ እየተጠባበቀ ቃላት መወራወር ውስጥ እንዲገባ አለፍ ሲልም ደም አፋሳሺ ወደ ሆነ ነውጥ እንዲያመሩ ያደርጋቸዋልም ነው ያሉት፡፡
ኮምሽነር ዮናስ አዳዬን ችግራቸውን ተቀራርበው በመፍታት የአገራቸውን ምጣኔ ሃብት ካሳደጉ አገራት ተሞክሮ በመውስድ ሀገር ማስቀጠል ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅ ሥራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዙፋን አምባቸው