ነሀሴ 21/2013 (ዋልታ) – የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጎ ኦባሳንጆን የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ አድርጎ ሾመ።
የአንጋፋው ፖለቲከኛ በቀጠናው መሾም የአፍሪካ ህብረት በመላው የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሰላምን፣ደህንነት እና አካባቢያዊ መረጋጋት እንዲሰፍን ካለው ቁርጠኝነት ነው ተብሏል።
የኦሊሴጎ ኦባሳንጆ በተለይም ከሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር በቀንዱ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ያስችላሉ።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት ኦሊሴጎ ኦባሳንጆ የህብረቱ የጋራ ፍላጎትን ለማሳካት ሲባል ይህን ስትራቴጂካዊ የፖለቲካ ተልዕኮ በመቀበላቸው አመስግነዋል።
ምዕራብ አፍሪካዊቷን ሀገር ናይጄሪያን ለ8 አመታት የመሩት ኦባሳንጆ ለረጅም አመታት ያካበቱትን የፖለቲካ ልምድ በመጠቀም የአፍሪካ ቀንድ ውህደትን ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደሚያሳድጉት ተነግሯል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁሉንም አይነት ድጋፍ ለከፍተኛ ተወካዩ እንዲያደርግ ህብረቱ ጥሪ አቅርቧል።
አዲሱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን አባሳንጆ በሚቀጥሉት ሳምንታት ወደ ክልሉ እንደሚደርሱ የአፍሪካ ህብረት አስታውቋል።