“ኦሮ-ፍሬሽ” አክስዮን ማህበር የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶችን ለአዲስ አበባ ነዋሪዋች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ጀመረ

“ኦሮ-ፍሬሽ” አክስዮን ማህበር

ጥቅምት 27/2014 (ዋልታ) “ኦሮ-ፍሬሽ” የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ አክስዮን ማህበር በዛሬው እለት የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬ ምርትችን ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለገብያ ማቅረብ ጀመረ።

አክሲዮን ማህበሩ አምራቹን ቀጥታ ከሸማቹ ጋር ለማገናኘት  የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለአዲስ አበባ ገበያ እንደሚያቀርብ መገለጹ ይታወሳል።

በዛሬው እለትም የኦሮ ፍሬሽ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ አክስዮን ማህበር በአዲስ አበባ ሳር ቤት የአትክልትና ፍራፍሬ ሽያጭ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እያካሄደ ይገኛል።

ዓላማው አምራቾች በቀላሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በቀጥታ ለሸማቹ ህብረተሰብ ለማድረስ ያለመ ነው።

ተቋሙ ምርቱን ለሸማቹ በቀጥታ በማቅረብ የገበያ ሰንሰለትን ማሳጠርና ገበያን የማረጋጋት ዓላማዎችን ይዟል።

የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ስራ ዪኒየን፣ መቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ ህብረት ስራ ዪኒየን እና ሌሎች ህብረት ስራ ማህበራት ተሳትፈዋል።

ገቢያውም ቅዳሜ እና እሁድ በየአካባቢው የሚቀርብ ሲሆን ድንች፣ ሽንኩርት፣ ቡና፣ ቲማቲም፣ ሀባብ እና ሌሎች ምርቶች ናቸው ለግብይት የሚቀርቡት።

በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ  ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች እና ሸማቾች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።