ከሀገር እስከ ደጀን የኢትዮጵያ ሰራዊት ነን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ኅዳር 6/2014 (ዋልታ) በመዲናዋ ከ200 ሺሕ በላይ ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ጸጥታ ለሚጠብቁ የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና መሰጠት መጀመሩን የአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከሀገር እስከ ደጀን የኢትዮጵያ ሰራዊት ነን ያሉት ከንቲባዋ ሰልጣኞቹ የጠላትን ፕሮፖጋንዳ ተረድቶ የሚያከሽፍ ለከተማዋ የሰላም ዘብ መሆናቸውን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱብንን ሁሉ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ሴራቸውን በማፍረስ በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን አደጋ በብቃት መመከት ይገባልም ብለዋል፡፡
ለዚህም የከተማችንን ብሎም የኢትዮጵያችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የከተማችን ነዋሪዎች ‹‹እኔም የሰፈሬ ፖሊስና የሰላም ዘብ ነኝ!›› በማለት በእልህና በቁርጠኝነት ተነስተዋል ነው ያሉት፡፡
ስራቸው ውጤታማ እንዲሆንም ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ትብብር እና ድጋፍ እንዲደርጉ ከንቲባዋ አሳስበዋል፡፡