ከሀገር የተሰደዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን መንግስት ጋር እየሰራ ነው -አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ

የተጎዱ እና ከሀገር የተሰደዱት ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን መንግስት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ገለጹ፡፡

አምባሳደር ይበልጣል በአል አረብያ አልሃዳድ ቴሌቪዥን ቀርበው በትግራይ ስለተከሰቱት የቅርብ ጊዜ ክስተቶች ዙሪያ ንግግር አድርገዋል፡፡

ህውሀት በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት የፈጸመውን የክህደት ተግባር ተከትሎ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሲባል የተወሰደው ሕግ ማስከበር እርምጃ አግባብነት ያለው መሆኑን አምባሳደሩ አስታውቀዋል፡፡

አሁን ላይ የህግ ማስከበር ተልዕኮው ተጠናቆ ወንጀለኞችን ወደ ህግ የማቅረብ ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ የመንግሥት ዋና ትኩረት የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባትና ለችግረኞች ሰብዓዊ ዕርዳታ መስጠት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የህወሃት ቡድን ላለፉት ሁለት ዓመታት ልዩነቶችን ለመፍታት በርካታ የቀረቡለትን የድርድር ጥያቄዎች አለመቀበሉንም ገልጸዋል፡፡