ከሃይማኖት አባቶች ጋር ሀገራዊ የምክክር መድረክ ተካሄደ

ጥር 24/2014 ዋልታ) “ማኅበራዊ ሃብቶቻችን ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ ሀሳብ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ሀገራዊ የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
በመድረኩ በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ኢትዮጵያዊያን ሌሎች ሊማሩበት የሚችሉ ትልቅ ማኅበራዊ እሴቶች እንዳሏቸው ገልጸው ከነዚህም እሴቶች አንዱ በሃይማኖት መካከል ያለውን ቅርርብ ማጠናከር የሚያስችለው በሃይማኖቶች መካከል ያለው መከባበር መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ለማስረፅ የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው ሕዝብና መንግሥትን ለማጋጨት የሃይማኖትን ጭምብል ለብሰውና ሃይማኖትን ተገን በማድረግ የሀገርን ሰላም እያደፈረሱ ያሉ አካላት ላይ መንግሥት እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶች የሃይማኖት አብሮነትና መከባበር እሴቶችን ለወጣቶች በማስተማር ወጣቱ የሰላም ዘብ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡