ነሐሴ 30/2014 (ዋልታ) የወቅቱ ዝናብ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ከመስከረም የመጀመሪያው አሥር ቀናት ጀምሮ እየቀነሰ እንደሚሄድ የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢኒስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢኒስቲትዩቱ የወቅቱ ዝናብ ሰጭ የሚቲዮሮሎጂ ገጽታዎች ከመስከረም ከመጀመሪያው አሥር ቀናት ጀምሮ ከሰሜን ምሥራቅና ከሰሜን ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ እየተዳከመ ወደ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብና በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ገልጿል፡፡
በወሩ መጨረሻ ሳምንት ደግሞ የሰሜን ምሥራቅ፣ የምሥራቅና የመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች በበጋው ደረቅ የአየር ጠባይ ተጽዕኖ ሥር መሆን ይጀምራሉ ብሏል፡፡
በመጪው መስከረም ወር በፀሐይ ኃይል ታግዘው ከሚፈጠሩ የደመና ክምችቶች በአንዳንድ የሰሜን ምዕራብ፣ የምዕራብና የመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ነጎድጓዳማ የአየር ሁኔታን በማስከተል ከባድ ዝናብና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል እንደሚችልም የትንበያ መረጃዎች ጠቅሶ ኢኒስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
በተለይም ከወሩ አጋማሽ በኋላ አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት ዝናብ ሰጭ የሚቲዮሮሎጂ ገጽታዎች ለረጅም ጊዜ ደረቅ ሆነው በሰነበቱት የደቡብ ኦሮሚያና የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ቦታዎች ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ ሁሉም የትግራይ ዞኖች፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የጋምቤላ፣ የአማራ ክልል፣ ከአፋር ክልል ዞን 3 እና 5፣ ከኦሮሚያ ክልል ሁሉም የወለጋና የሸዋ ዞኖች፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ቡኖ በደሌ በአብዛኛው መደበኛና ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡
እንዲሁም የአርሲ ዞኖች፣ አዲስ አበባ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ አብዛኛው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል እና የሲዳማ ክልል ዞኖች በአብዛኛው መደበኛና ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚያገኙ ከኢኒስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡