ከምርጫ ድል በላይ ሀገር እና ህዝብ ይቀድማል – የኦሮሚያ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክክር መድረክ


ሰኔ 20/2013 (ዋልታ) – ከምርጫ ድል በላይ አገርና ህዝብ ይቀድማል ሲል የኦሮሚያ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክክር መድረክ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫን አፈፃፀም በተመለከተ በዛሬው እለት መግለጫ ሠጥቷል።
ሰኔ 14/2013 በተካሔደው 6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቅድመ ምርጫ አንስቶ እስከ ምርጫው እለት ከፖርቲዎች የቀረቡለትን ቅሬታዎች በወቅቱና በአግባቡ በመለየት ቅሬታዎች እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራቱን የጋራ ምክክር መድረኩ በመግለጫው አስታውቋል።
ለዚህም ምርጫውን በንቃት የሚከታተል እና ቅሬታዎችን የሚቀበል እና የሚፈታ አንድ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ ሲሠራ እንደነበር ተገለጸ ሲሆን በዚህም አመርቂ ውጤት ተገኝቷል ተብሏል።
የምርጫ የጣቢያ የምርጫ አስፈፃሚዎች አፈፃፀም ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮች፣ ከታዛቢ አቅርቦት እና ከቁሳቁስ አቅርቦት ጋር የተያያዙ እና መሠል ችግሮች በምርጫው ወቅት ያጋጠሙ መሆናቸውን የጋራ ምክክር መድረኩ በመግለጫው የገለፀ ሲሆን ምክክር መድረኩ ባለው የመገናኛ መረብ አማካኝነት በእለቱ የመፍታት ስራ መሠራቱን የጋራ ምክክር መድረኩ ሰብሳቢ አቶ ከድር ማሞ እና የምክክር መድረኩ ፀሐፊ አቶ አስናቀ ሸንገማ ገልፀዋል።
መድረኩ አባል ፖርቲ የሆኑት የእናት፣ የኢዜማ፣ ብሔራዊ አንድነት፣ የብልፅግና እና ሌሎች የምክክር መድረኩ አባል ፖርቲ ተወካዮች በመግለጫው ላይ እንደገለፁት ምርጫው ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ዲሞክራሲያዊ እና ነፃ ሆኖ የተጠናቀቀ ነው ብለዋል።
ከውጭም ከውስጥም የሀገሪቷን ሠላም ለማወክ በሚሰሩበት በዚህ ወቅት ህዝቡ በራሱ ድምፅ መንግስትን ለመመስረት ያሳየው ትጋት እና ጨዋነት የሚመሰገን ነው ሲሉም ፖርቲዎቹ ህዝቡን እና የፀጥታ አካላትን ጨምሮ ምርጫ ቦርድንም በመግለጫቸው አመስግነዋል።
ከምርጫ ድል በላይ ሀገርና ህዝብ ይቀድማል እና ኢትዮጵያን በማስቀደም ካሸነፈው የፖለቲካ ፖርቲ ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም የኦሮሚያ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክክር መድረክ አባል ፖርቲዎች አስታውቀዋል።
እንደ ኦሮሚያ የተፎካካሪ ፖርቲዎች የጋራ የምክክር መድረክ በቀጣይ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ከምርጫው ሊወሠዱ ይገባል ያሏቸውን ምክረ ሀሳቦችንም በመግለጫው ላይ ገልጿል።
ተፎካካሪ ፖርቲዎች ተቀራርበው በመነጋገር፣ አብሮ በመስራትና በመቻቻል የሚፈጠሩ ችግሮችንም ህግን እና ስርዓትን በተከተለ አግባብ ብቻ የሚፈቱበትን መንገድ ማጎልበትን ከዘንድሮው ምርጫ ሊወስዱ ይገባል ሲሉም አሳስቧል።
በምርጫው የተሳተፋ ተፎካካሪ ፖርቲዎች እየገለፁ ባሉት ቃል መሰረት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚያሳውቀውን የምርጫ ውጤት በመቀበል ቅሬታም ካለ ህጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ ማቅረብ እንደሚኖርባቸውም የኦሮሚያ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክክር መድረክ አሳስቧል።
(በድልአብ ለማ)