ከምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል አባል አገራት የተውጣጡ ወጣቶች በእንጦጦ ፓርክ ችግኝ ተከሉ

ሰኔ 30/2013 (ዋልታ) – ከምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል አባል አገራት የተውጣጡ ወጣቶች በአዲስ አበባ እንጦጦ ፓርክ ችግኝ ተከሉ።

በምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል አዘጋጅነት የአባል አገራቱ ወጣቶች በሰላም ላይ ያተኮረ ልምድ ልውውጥና ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

ወጣቶቹ በትናንትናው እለት በቀጣናው ሰላምና ወቅታዊ ሁኔታ የወጣቶች ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገዋል።

ዛሬ በተደረገው የመርሃ ግብር መዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ ወጣቶቹ በእንጦጦ ፓርክ ችግኝ የተከሉ ሲሆን የተጠባባቂ ሃይሉን ዳይረከተር ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም ተገኝተዋል።

የተጠባባቂ ሃይሉ ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ጌታቸው ሽፈራው፤ ”የአረንጓዴ አሻራ በማሳረፋችን ኮርተናል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም የተጠባባቂ ሃይሉ አባል አገራት ወጣቶች የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ አካል እንዲሆኑ በመፍቀዱ ይመሰገናል ነው ያሉት።

የአረንጓዴ አሻራ ተግባር በአባል አገራቱ ዘንድም እንዲስፋፋ ጥረታቸውን እንደሚያጠናክሩ ነው የገለጹት።

የግብርና ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለግብርና ዘርፍ ካለው ጠቀሜታ አንጻር እየተሰራ ያለው ስራ የሚደገፍ ነው ብለዋል።

ችግኝ የምግብ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ የቤተሰብ የሀይል ፍላጎት ማሟያ ሆኖም የሚያገለግል በመሆኑ የተጀመረው ጥረት ይጠናከራል ብለዋል።

በዚህ ዓመትም ኢትዮጵያ 6 ቢሊዬን ችግኝ በአገር ውስጥ ለመትከል ማቀዷንና አንድ ቢሊዬን ደግሞ ለጎረቤት አገራት ማዘጋጀቷን ጠቅሰዋል።

ይህው እቅድ እንዲሳካ ወጣቶች የነገ ሕይወታቸው የተሻለ እንዲሆን ለዚህ በጎ ተግባር ሊረባረቡ ይገባልም ብለዋል።

የምሰራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሀይል አባል አገራት ወጣቶችም ኢትዮጵያ መጥተው ችግኝ በመትከላቸው ሊመሰገኑ ይግባል ነው ያሉት።

የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ህይወት ሀይሉ፤ ችግኝ ተካላ የድንበር ተሻጋሪ በጎ ፈቃ አገልግሎት አካል መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲህ አይነት ተግባር ጠቃሚና የጋራ ግንኙነትን ከማጠናከር ባሻገር ትስስርም የሚያበረታ በመሆኑ ሊለመድ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶችም በሌሎች የቀጣናው አገራት ተዘዋውረው ችግኝ መትከልና ለሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ እቅድ መኖሩን ገልጸዋል።

ብሩንዳዊቷ ወጣት አይሚ ንሽሚርማናና ኬኒያዊው ወጣት አለን ሩቶ ”ወጣቶች ከምንም በላይ ለቀጠናው ሰለም መቆም አለባቸው” ይላሉ።

ይህ ሲሆን ለነገ ሕይወታቸው የተሻለ የሚያደርጉባቸው መንገዶች ላይ ማተኮር እንደማያቅታቸውም ይናገራሉ።

ለዚህ ደግሞ የአካባቢ ጥበቃ ማድረግና ችግኝ መትከል የዘውተር ተግባር ቢሆን የተሻለ መሆኑን ይመክራሉ።

እንደ ኢዜአ ዘገባ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል 10 አገራትን በአባልነት የያዘ ሲሆን, በሰላምና ደህንነት ላይ አተኩሮ የሚሰራ ተቋም ነው።