ከምዕራብ ወለጋ ዞን ከ43 ሺሕ ቶን በላይ ቡና ለምርት ገበያ ቀረበ

ግንቦት 26/2014 (ዋልታ) በምዕራብ ወለጋ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ43 ሺሕ ቶን በላይ ቡና ለምርት ገበያ መቅረቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽሕፈት ቤቱ የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ቡድን መሪ ኤፍሬም መስፍን እንደገለጹት በዞኑ ቡናን በተሻለ በማምረት አርሶ አደሩ የልፋቱ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነው፡፡

የአካባቢው አርሶ አደር ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ቡና ያምርት እንጂ የልፋቱን ያህል ተጠቃሚ እንዳልነበር ያስታወሱት የቡድን መሪው፣ አሁን ግን ምርቱን በቀጥታ ወደ ምርት ገበያ ማቅረብ በመጀመሩ የተሻለ ዋጋ እያገኘ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

በዞኑ ቡና ከአርሶ አደሩ ገዝተው ለምርት ገበያ የሚያቀርቡ 982 ነጋዴዎች፣ 4 የገበሬዎች ሕብረት ስራ ዩኒየኖችና 2 ሃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ኩባንያዎች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡

በእነዚህና በአርሶ አደሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 43 ሺሕ 407 ቶን የታጠበና ያልታጠበ ቡና ለምርት ገበያ መቅረቡንም አመልክተዋል።

አምና በተመሳሳይ ወቅት 38 ሺሕ 927 ቶን የታጠበና ያልታጠበ ቡና ለምርት ገበያ የቀረበ ሲሆን የዘንድሮው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር በ4 ሺሕ 480 ቶን ብልጫ አንዳለውም አብራርተዋል፡፡

በዞኑ በቡና ከተሸፈነው 489 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት 70 በመቶ ምርት እየሰጠ መሆኑን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘውን መረጃ ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው።