ከሰሞነኛው የአልሸባብ ጥቃት ጀርባ ያለው እውነታ ምንድን ነው?

በደረሰ አማረ

ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) ለዘመናት ያለማቋረጥ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ጥቃት የሚደርስበት ለምንድን ነው? ስለምን የኢትዮጵያ ጠላቶች አሁን ላይ እንደ አሸን ፈሉ? የሚለው ጥያቄ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የሚመጥን ነው፡፡

ከምዕራቡ ዓለም እስከ መካከለኛው ምስራቅ፣ ከሰሜን አፍሪካ እስከ ጎረቤት ሀገራት የተዘረጋው ኢትዮጵያን የማዳከም ፕሮጀክት ከተጠነሰሰ ረጅም ዓመታት አስቆጥሯል፡፡

በኢትዮጵያ ውጫዊ ጠላቶች እና በውስጥ ባንዳዎች በቅንጅት የተዘረጋው ኢትዮጵያን የማዳከም ፕሮጀክት ከተቻለም ሀገሪቱን እስከ መበታተን  ይዘልቃል፡፡

ኢትዮጵያን ለማዳከምም የተከፈተው ዘመቻ መልከ ብዙ ሲሆን ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የመረጃ ጦርነቶችን ያካተተው ነው፡፡

እነዚህ መልከ ብዙ ሁኔታዎች ጠቅለል ተደርገው ግራጫው ጦርነት  በመባል  ይጠራሉ፡፡

በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የሌክሲንግተን ኢንስቲትዩት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪ ቴዎዶር ካራሲክ (ፒኤችዲ) “አልሸባብ ከሰሞኑ በሶማሊያ እና በምስራቅ ኢትዮጵያ የድንበር አካባቢዎች ስለምን ጥቃት መፈፀምን ፈለገ?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ከፍተኛ አማካሪው ጥቃቱን አስመልክተው ባወጡት ዘለግ ያለ ትንታኔያቸው ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡

አንድም የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በምርጫ ወደ ስልጣን መምጣተቸውን ተከትሎ፤ ሶማሊያን ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ማዋሀድን ቅድሚያ መስጠታቸው በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ ከሚል ስጋት የመነጨ  ሊሆን እንደሚችል አስምረውበታል ፡፡

የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ስልጣን በያዙ ማግስት በቀጣናው ሀገራት ጉብኝት በማድረግ ሀገራቸው በቀጣናው ወደፊት ሊፈጠር ከሚችል በጎ እድል ተቋዳሽ እንድትሆን በማሰብ ከሰባቱ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ (ኢስት አፍሪካን ኮሚዩኒቲ) መካከል አንዷ እንድትሆን ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

“ይህ የሱማሊያ ጥያቄ ከተሳካ የሽብር ቡድኑ በምስራቅ አፍሪካ ያለው ህልውና እስከ ወዲያኛው እንደሚያከትም በማመኑ  የፕሬዝዳንት ሀሰን ሼህ መሀመድን ጥረት ለማደናቀፍ ጥቃትን ምርጫው አድርጓል” ሲሉ ዶ/ር ካራሲክ በትንታኔ ጽሁፋቸው ይሞግታሉ፡፡

አልሸባብ ይህንን ዓላማውን ማሳካት ከቻለ የአፍረካ ቀንድ እንደታመሰ፤ ይቀጥላል ሱማሊያም መደበቂያው እንደሆነች ትቀጥላለች ማለት ነው፡፡

በሌላም በኩል ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ  እና ሱማሊያ የአልሸባብን እንቅስቃሴ ለመገደብ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪው፤ ኢትዮጵያ የሽብር ቡድኑን ጥቃት ለመከላከል “የፀጥታ ጥበቃ ቀጠና” ለመፍጠር እንቅስቃሴ ላይ መሆኗ አልሸባብን እንቅልፍ እንደነሳው ገልፀዋል፡፡

በዚህም ይህን የፀጥታ ጥበቃ ቀጠና ለመስበር ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ፤ የደረሰበትን የአፀፋ እርምጃ መቋቋም ተስኖት ማፈግፈጉን አስታውሰዋል፡፡

ሌላኛው ኬኒያ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳንን በወደብ እና በትራንስፖርት አገልግሎት ለማስተሳሰር የተነደፈውን የምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የመሰረተ ልማት ተነሳሽነት (LAPSSET) ፕሮጀክት ጋር ይገናኛል ይላሉ፡፡

እንደ LAPSSET ያሉ ፕሮጀክቶች ወደብ አልባ ለሆኑ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ መሆናቸው ቡድኑን ለጥቃት እንዳነሳሳው ነው የገለፁት፡፡

በዚህም በአካባቢው መጠነ ሰፊ ጥቃትና ሽብር በመፍጠር የግንባታ ተቋራጮች እንዲሸሹ በማድረግ በርካታ የLAPSET ፕሮጀክቶች እዲቆሙ አልሸባብ ያለ የሌለ አቅሙን እየተጠቀመ ይገኛል ብለዋል፡፡

እነዚህ የሀገራቱን ትስስር የሚያጠናክሩ ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ ከተፈለገ በአል-ሸባብ ላይ የጋራ ፀረ-ሽብር ዘመቻ አስፈላጊ እንደሆነም ምሁሩ በፅሑፋቸው መክረዋል ።

በእርግጥም እንደ አልሸባብ ያሉ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖችን እንቅስቃሴ ከምንጩ ለማድረቅ የአካባቢው ሀገራትና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ ትልቅ መሆን እንደሚገባው ቢታመንም፤ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ህልውና ላይ የተከፈተውን ግልጽና ረቂቅ ዘመቻ ለመመከት፤ በሁሉም ግንባሮች የሚቃጡ ብሔራዊ ጥቃቶችን ለመቀልበስ፤ ብሎም በዘላቂነት የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለማረጋገጥ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን በማጠናከር በጋራ መቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያን የመበተኑ ፕሮጀክት አድማሱ ሰፊ መሆኑን ለመረዳት ሰሞኑን አልሸባባር በሞከረው ጥቃት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መሳተፋቸው፣ ኦነግ ሸኔ ከጋምቤላ ነጻ አውጪ እና ከትሕነግ ጋር እየሰራ መሆኑን በይፋ መግለጹን ስናክልበት የኢትዮጵያ ጠላቶች ሀገሪቷን ለማዳከም በሁሉም አቅጣጫ ተባብረው እየሰሩ እንደሆነ እንረዳለን፡፡

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመሆን የሚያካሂዱት ግራጫው ጦርነት እልህ አስጨራሽ ነው፡፡

እነዚህ ጠላቶች የጦርነቱን ጊዜ በማራዘም ውጤት ለማግኘት ያለሙ በመሆናቸው የኢትዮጵያዊያንን ፅናት የሚፈታተን ሊሆን ቢችልም፤ ኢትዮጵያውያን በጽናት እና በጋራ በመቆም ተልእኮዎቻቸውን ማክሽፍ ይኖርባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያን ከተጋረጡባት አደጋዎች በዘላቂነት ሊቀለብስ የማይችል አካሄድ ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ  የሽብር ቡድኖች እድሜያቸውን የሚያረዝሙበትን ምክንያት እንዲያገኙ መፍቀድ  ይሆናል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያን በዘላቂነት አሸናፊ በሚያደርግ አካሄድ ላይ ኢትየጵያውያን በቅንጅት መስራት ይገባቸዋል፡፡