መጋቢት 1/2015 (ዋልታ) ከሰሞኑ ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች ላይ ያልተጠበቀ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች ዘመናዊዎቹን ኪንዝሃል ሚሳኤል በመጠቀም ጭምር ነው የፈፅመችው፡፡
ሩሲያ በጥቃቷ በበርካታ የዩክሬን ከተሞች ላይ ጉዳት ያደረሰች ሲሆን ከ81 በላይ ሚሳኤሎችን ወደ ዩክሬን አስወንጭፋለች፡፡
እንደ አልጀዚራ ዘገባ በጥቃቱ ጥቅም ላይ ከዋሉ መካከል ስድስቱ ኪንዝሃል የተሰኙ ሃይፐር ሶኒክ ሚሳኤሎች ናቸው፡፡
ኪንዛሃል የተሰኙት እነዚህ ዘመናዊ ሚሳኤሎች ከድምጽ ፍጥነት በአስር እጥፍ የሚበልጡ ፍጥነት ሲኖራቸው በሰዓት 12 ሺሕ ኪ.ሜ ይምዘገዘጋሉ፡፡ ይህም ፍጥነት የራዳር ሲስተሞችን ሳይቀር ጥሶ መግባት የሚችል ነው ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሚሳኤሎቹ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን መሸከም የሚችሉ ሲሆኑ እስከ 2 ሺሕ ኪ.ሜ ርቀት ድረስ ያሉ ኢላማዎችን ድባቅ ይመታሉ ተብሏል፡፡
ሚሳኤሎቹ 480 ኪሎ ግራም ክብደት እንዳላቸውም ተጠቁሟል፡፡
የዩክሬን አየር ኃይል ቃል አቀባይ ዩሪ ኢህናት ሀገራችን እነዚህን ኪንዝሃል ሚሳኤሎችን ለመከላከል አቅም የላትም ማለታቸውን ዘገባው አመላክቷል፡፡
በሳሙኤል ሙሉጌታ