ከተማ አስተዳደሩ ለጋምቤላ ክልል ባህል ማዕከል ግንባታ የ5 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ አበረከተ

የካቲት 20/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጋምቤላ ክልል ለባህል ማዕከል ግንባታ የ5 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ርክክብ አድርጓል፡፡

በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዑመድ ኡጁሉ ከተማ አስተዳደሩ ያበረከተዉ ቦታ የጋምቤላን ሕዝብ ባህል፣ ወግ፣ ልማድና ትውፊት በአግባቡ በመሰነድ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማስተዋወቅ የሚረዳ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የባህል ማዕከሉ በአዲስ አበባ መገንባቱ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ቱሪስቶች በቀላሉ የጋምቤላን ባህል በመዲናዋ በመጎብኘት ለሀገሪቱ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

አሸባሪው ሕወሓት በተለያዩ ክልሎች ባህሎች ጎልተው እንዳይወጡ ካደረጋቸው ክልሎች አንዱ የጋምቤላ ክልል መሆኑን ገልፀው የከተማ አስተዳደሩ ላበረከተ ቦታ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ቤት መሆኗን ገልጸው ለክልሉ የተበረከተው የባህል ማዕከል ግንባታ ቦታ የጋምቤላን ባህልና ወግ ከማስፋፋትና ከማሳወቅ ባሻገር አዲስ አበባን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ በበኩላቸው የባህል ማዕከሉ በመዲናዋ መገንባት አዲስ አበባ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የስበት ማዕከል በመሆኗ በሁሉም ዘርፍ ክልሉ እንዲያድግ ይረዳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሥነሥርዓቱ ላይ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ባንቻየሁ ድንጋታን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት