ከተማ አስተዳደሩ ቢሾፍቱ ለሚገኘው የመከላከያ ሆስፒታል የ15 ሚሊዮን ብር የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ጥቅምት 28/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሾፍቱ ለሚገኘው የመከላከያ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስና የአልባሳት ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን ቢሾፍቱ በሚገኘው ሆስፒታል ያስረከቡት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ናቸው።
የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተጎዱ ጀግኖችን ማከም ትልቅ ክብር የሚያስገኝ መሆኑ በዚህ ረገድ የሕክምና ድጋፍ እያደረጉ ላሉ ባለሙያዎች ከንቲባዋ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ለአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ እንደ ግዴታ እንጂ እንደ መብት መታየት እንደሌለበትም ገልጸዋል።
በሆስፒታሉ ላለው የሕክምና ባለሙያዎች እጥረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እገዛ ለማድረግ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች ተናግረዋል።
የመከላከያ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተገኝ ለታ የከተማ አስተዳደሩ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
ድጋፉ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ጠቅሰው መሰል ድጋፎች የአገር መከላከያ ሰራዊትን የግዳጅ አፈጻጸም እንዲጠናከር አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ሌሎችም ለመከለከያ ሰራዊት የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።