ከተማ አስተዳደሩ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር የሥራ ትውውቅ መድረክ አካሄደ

ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባላት ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር የሥራ ትውውቅ እንዲሁም ቀጣይ በከተማዋ ስለሚያከናውኑት ተግባራት እና መንግሥት እንደ አንድ ባለድርሻ አካለት የሚጠበቅበትን ሚናዎች አስመልክቶ የጋራ ውይይት በዛሬው ዕለት አድርገዋል።

የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር በሚደረገው ሀገራዊ ውይይት የከተማው ሕዝብ በአግባቡ ተወክሎ እንዲወያይ እንዲሁም እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል በአግባቡ እንዲወከል እንደ ከተማ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል።

በዚህ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይ ተስፋ ብቻ ሳይሆን እምነትም ጭምር አለን ያሉት ከንቲባዋ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ በሆነ መንገድ ካወያዩት ወደ መግባባት እና ወደ አንድነት የማይመጣበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ገልጸዋል።

“የምትሄዱበት መንገድ ቀላል ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን አዲስ ምዕራፍ በሀገራችን ለመጻፍ፣ አሻራችሁን ለማኖር በውይይት የሚያምን ትውልድ ለመገንባት የኮሚሽኑ አባላት ትልቅ ልምድ እና እውቀት ያላችሁ በመሆናችሁ እንደሚሳካላችሁ እኔ በግሌ ትልቅ እምነት አለኝ” ሲሉም ተናግረዋል።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በበኩላቸው የምክክር ኮሚሽኑ ከእርቀ ሰላም ኮሚሽን በተለየ በአዋጅ ከተቋቋመት አጀንዳዎች በዋናነት ከኅብረተሰቡ መጥተው ውይይት ተደርጎባቸው የጋራ መግባባትን ማምጣት መሆኑን መጠቆማቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ ሂሩት ገብረስላሴ በበኩላቸው የኮሚሽኑ ዋና ተግባር የምክክር መድረኮችን ማመቻቸትና ምክክሩ ምክክሩ አሳታፊና አካታች እንዲሆን ማድረግ ነው ያሉ ሲሆን አጀንዳውን የሚወስነው ከታች ጀምሮ በሚገባ እንዲወከል በሚደረገው ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡
በከተማው የሚገኙ አስተዳደራዊ ተቋማት የኮሚሽኑን ተልእኮ ለማሳካት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያለምንም ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ እንዲያከናውኑም በከንቲባ አዳነች አቤቤ አቅጣጫ መቀመጡ ተገልጿል፡፡