ከተሞቻችን – ጅግጅጋ


የምስራቋ ፈርጥ፣ የብዙኃን መናህሪያ እና የእንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ምድር የሆነችው የጅግጅጋ ከተማ ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተምስራቅ አቅጣጫ 618 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

በአብዛኛው ሜዳማ ተፈጥሯዊ የመሬት ገፅታ የተጎናጸፈችው ይህች ከተማ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና መቀመጫ ናት፡፡

ከባህር ጠለል በላይ 1ሺሕ 609 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ጅግጅጋ ሞቃታማ የአየር ንብረት አላት፡፡ ከተማዋ በ1916 ዓ.ም በፊታውራሪ ተክለ ሐዋሪያት ተክለ ማርያም እንደተመሰረተች ይነገራል።

ጅግጅጋ የሚለው ቃል መነሻው ሕዝቡ የውሃ ጉድጓዶች ሲቆፍር ከተሰሙ የተለያዩ የ”ጂግ-ጂግ” ድምፆች መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በአካባቢው ማኅበረሰብ “ላአ” ተብሎ ይጠራ እንደነበር እና ይህም በሶማሌ ቋንቋ “ማራኪ እይታ” ማለት እንደሆነ ይነገራል።

የካራማራ ሰንሰለታማ ተራራ ከጂግጂጋ ከተማ በ12 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ውብ እና አረንጓዴ መልከዓ ምድራዊ ተፈጥሮ ያለው ይህ ተራራ የካራማራ የድል ብስራት ህያው ምስክርም ጭምር ነው።

ጅግጅጋ በአራት ክፍለ ከተማ እና ሀያ ቀበሌዎች የተዋቀረች ስትሆን ክፍለ ከተማዎቿ ካራማርዳ፣ ዱዳሂዲ፣ ጋራብአሴ እና ቆርዴሬ ይባላሉ፡፡

በሱማሌ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ያላቸው የሰዒድ መሀመድ አብደላ ሀሰን መታሰቢያ የሆነ ሀውልት በከተማዋ አማካኝ ስፍራ ላይ ይገኛል።

በከተማዋ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት ያሉ ሲሆን ጂግጅጋ ኢንተርናሽናል፣ አህመድ ጉራይ 1ኛ ደረጃ፣ ሺኽ አብዲ ሰላም ትምህርት ቤት፣ አፍላኸ 1ኛ ደረጃ፣ ሊበርቲ ኮሌጅ እና ጅግጂጋ ዩኒቨርስቲ ተጠቃሾች ናቸው።

የማያቋርጥና ፈጣን የንግድ እንቅስቃሴ ያላት ጅግጅጋ በአቅራቢያዋ ካሉ ወደብ ከተማዎች ከሚገቡ የኤሌክትሮኒክስ እና አልባሳት ንግድ በተጨማሪ በአውራ ጎዳና ላይ በሚከናወን የወርቅ ግብይትም ትታወቃለች።

የሶማሌ ባህላዊ ምግቦች የሆኑት ሀንጃሮ(ኪቢስሌ)፣ ሰባያድ እና መለዋን ጨምሮ ሌሎች ጣፋጭ ምግቦች በከተማዋ የሚታወቁ ሲሆን ሻይ በግመል ወተት ተወዳጅ የማህበረሰቡ መጠጥ ነው።

ጅግጅጋ በህክምናው ዘርፍ ትልቅ ስራን ለአለም ያበረከተውን ዶ/ር አክሊሉ ለማን ጨማሮ ድምፃዊ እዮብ መኮንን፣ ፀሀፊ ነጋ መዝለቂያ እና ሌሎችንም ብዙ የሀገር ባለውለታዎችን ያፈራች ድንቅ ምድር ናት።

ጅግጅጋ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁም ሆነ በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁባት ትዝታችሁን አጋሩን። መልካም ሳምንት!!

በአዲስዓለም ግደይ