ከተሾሙት አምባሳደሮች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በዲፕሎማሲው መስክ ያገለገሉ መሆናቸው ተገለጸ

ጥር 19/2014 (ዋልታ) ከተሾሙት 27 አምባሳደሮች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዲፕሎማሲው መስክ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ።

ቃል አቀባዩ በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአምባሳደርነት ሹመት ያገኙት ሙያዊ የሆነ ክህሎትና እውቀትን መሰረት በማድረግ ነው ብለዋል።

ሹመቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ ክብር ማስጠበቅ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ከተሾሙት አምባሳደሮች መካከል መኖሪያቸወን ኢትዮጵያ አድርገው የአምባሳደርነት ሥራቸውን የሚሰሩ እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሩ ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮን መነሻ በማድረግ ወጪን መቀነስ በሚያስችል መልኩ ሥራና ሰራተኛን ማመጣጠን የሚያስችል ነው ብለዋል።

በቅርቡ የአሜሪካ የአፍረካ ጉዳይ ተወካይ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የኢትዮጵያና የአሜሪካን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ወደ ነበረበት መመለስ የሚያስችል ሥራ ይሰራሉ ተብሎ ይጠበቃልም ነው ያሉት፡፡

በህግ ማስከበር ሂደቱ ከአሜሪካ ጋር አለመግባባት የነበር ቢሆንም አሁን ላይ የኢትዮጵያን እውነታ መረዳት መጀመሯ አስረድተዋል፡፡

በአንዳንድ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር የድርድር ሀሳብ እየተነሳ ነው በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ መንግሥት ምንም አይነት የድርድር ሀሳብ የለውም ቡድኑ አሁንም የሽብር ቡድንነቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደጸደቀ ነው ብለዋል።