ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ በሚንቀሰቀሱ የተራድኦ ድርጅቶች እርምጃ ስለመውሰድ

አቶ ፋሲካው ሞላ

መስከረም 03/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ አንድነትና ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ ጉዳዮች እንዲሁም ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ በሚንቀሰቀሱ አንዳንድ የተራድኦ ድርጅቶች ላይ በቅርቡ የማስተካከያ እርምጃዎችን እንደሚወስድ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ የሀገሪቱን ህግና ሥርዓት ሳያከብሩ ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ በሚንቀሰቀሱ አንዳንድ የተራድኦ ድርጅቶች ላይ በቅርቡ እንደጥፋታቸው መጠን ከማስጠንቃቂያ ጀምሮ እስከማገድና ማፍረስ የሚደርሱ የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎች ይወሰዳሉ።

“የኢትዮጵን ሉዕላዊነት፣ አንድነትና ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ ጉዳዮች ላይ በሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ምህረት የለንም ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በእንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ የምንደረደርበት ሁኔታ በጭራሽ አይኖርም” ብለዋል።

የተወሰኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከሀገር ጥቅም ተፃራሪ በሆነ ጉዳይ ላይ እንደሚንቀሳቀሱ መረጃዎች አሉን ያሉት አቶ ፋሲካው፣ ድርጊቱ የሀገርን ጥቅም የሚጎዳ በመሆኑ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤ የማጣራቱን ስራ እንደጨረስን አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል ብለዋል።