ከንቲባዋ ሁለት ባለ 9 ወለል ዘመናዊ ሕንጻዎችንና የስራ ዕድል መፍጠሪያ ማዕከላትን መርቀው ለነዋሪዎች አስተላለፉ

ግንቦት 22/2016 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሁለት ባለ 9 ወለል ዘመናዊ ሕንጻዎችንና የስራ ዕድል መፍጠሪያ ማዕከላትን መርቀው ለ140 አቅመ ደካሞች እና አካል ጉዳተኛ ነዋሪዎች አስተላለፉ።

ህንጻዎቹ በልደታ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቆርቆሮ ሰፈር በሚባለው የተጎሳቆለ የመኖሪያ መንደር ይኖሩ ለነበሩ ነዋሪዎች የተላለፉ ሲሆን “በጎነት” ተብለው በተሰየሙ የመኖሪያ መንደር የተገነቡ መሆናቸውንም ከንቲባዋ ገልጸዋል።

ለአቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ማየት ለተሳናቸው፣ ለተለያየ ማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ እና በልማት ለተነሱ ነዋሪዎች ያስተላለፍናቸው ምቹ የመኖሪያ ቤቶች ሳሎን፣ መኝታ ቤት፣ የማብሰያ እና የመጸዳጃ እንዲሁም የመኝታ ክፍሎች ያላቸው ዘመናዊ ቤቶች ናቸው ብለዋል።

በዚህ የበጎነት መንደር ካስተላለፍናቸው የመኖሪያ ቤቶች ጋር በማቀናጀት የእናቶችን ጫና የሚያቀል የህጻናት ማቆያ፣ ለአካባቢው እናቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ፣ የሚሰሩ እጆችን ከስራ የሚያገናኙ የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎኖችን እንዲሁም የልብስ ስፌት ማሽኖችን አዘጋጅተን ለነዋሪዎቹ የስራ እድል ፈጥረናልም ነው ያሉት።

በመኖሪያ መንደሩ ቤት ለሰጠናቸው ማየት የተሳናቸው ነዋሪዎች እንቅስቃሴ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ኬኖች፣ ለአካል ጉዳተኛ ነዋሪዎች ደግሞ ክራንችና ዊልቸሮችን አዳርሰናል ሲሉም በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

ሰርቶ ካገኘው ላይ ለወገን በጎ ለመስራት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ቤቶቹን የገነባውን ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በራሴና በነዋሪዎቹ ስም እያመሰገንኩ፣ በጎነት አያጎድልምና ፈጣሪ ጨምሮ እንዲሰጠው እመኛለሁ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሚሰሩ ልማቶች ሁሉ ለሰው ልጆች ተስፋ የሚሰጡ እና የኑሮ ጫናን የሚያቃልሉ ይሆኑ ዘንድ ሰው ተኮርነታችን በተግባር የሚገለጽ ነው ሲሉም አክለዋል።