ከንቲባዋ ለ2 ሺሕ ዜጎች ማዕድ አጋሩ

ሚያዝያ 22/ 2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መጪውን የኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ለ2 ሺሕ ዜጎች ማዕድ አጋሩ፡፡
ከተማ አስተዳደሩ መጪውን የኢድ አልፈጥር በዓልና የረመዳን ፆም ፍቺ ምክንያት በማድረግ ከከተማ እስከ ብሎክ ድረስ 101 ሺሕ 480 ዜጎች ማዕድ አጋርቷል፡፡
የማእድ ማጋራት መርኃ ግብሩ ከተባባሪ አካላት ጋር በሚደረግ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት በዘላቂነት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ተብሏል።
ከንቲባ አዳነች በእኛ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንተ ትብስ በሚል የቆየውን የመከባበርና የመደጋገፍ እሴቶቻችንን በተግባር በመጠቀም ድጋፍ የሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ እርብርብ ማድረግ ይገባናል ብለዋል ፡፡
በመስጠታችን እንባረክ ይሆናል እንጂ አይጎድልብንም እንዲሁም ወንድማማችነትና አብሮነታችን ይጠነክራልም ብለዋል ከንቲባ አዳነች።
በዚሁ ወቅት ከንቲባዋ ከተማ አስተዳደሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚሰራቸው ስራዎችና በሚፈጥራቸው የሥራ ዕድሎች ሁሉ በመሳተፍ መንግስት እናንተን ለመደገፍ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ኑሯችሁን በዘላቂነት ለመቀየር መዘጋጀትና ማንኛውንም ሥራ ለመስራት መወሰን ይኖርባችኋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አስፋው ተክሌ በበኩላቸው እኔነትን በመተው፣ እኛነትን በመምረጥ ሕዝባዊ አንድነታችንን በማጽናት ወደ ፊት እየተደጋገፍን በአብሮነት መሻገር እንዲቻለን የነበሩንን አጠቃላይ በጎ ማሕበራዊ ዕሴቶቻችንን ወደ ተግባር እየለወጥን መደጋገፍ ይኖርብናል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ከሚያዝያ ወር የመጀመሪያ ቀናት አንስቶ ሲደረግ በቀየው የማዕድ ማጋራት መርኃ ግብር የዛሬውን ጨምሮ 341 ሺሕ 480 ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ተደርጓል የተባለ ሲሆን የከተማዋ ባለሃብቶችም በከፍተኛ ሃገራዊ ስሜት ምለሽ እየሰጡም ነው መባሉን ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡