ከንቲባዋ በልደታ ክ/ከተማ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ አስቀመጡ

ሰኔ 20/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ አስቀመጡ።

በአዲስ አበባ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ከንቲባዋ የከተማዋን ነዋሪዎች ጫና ለመቅረፍ በከተማ አስተዳደሩ በርካታ ተግባር ተኮር ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

የልማት ፕሮጀክት እቅዶች መካከል በሆነው የመኖሪያ ቤት ግንባታም የከተማዋን ነዋሪ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በዛሬው እለትም የልደታ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጌጃ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በርካታ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመኖሪያ ቤት ግንባታን አስጀምረዋል።

በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ በከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ያለውን ጥረት ሁሉም አካል እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።

በአጭር ጊዜ ግንባታ ለግልጋሎት የሚበቃው የመኖሪያ ቤት ግንባታም በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ከመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ከንቲባዋ ገልጸዋል።

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከወነ ያለው የፕሮጀክቶች ግንባታ ለነዋሪዎች ችግር ምላሽ ከመስጠት ባለፈ ለከተማ ገፅታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ነው የተባለው::

ከዚህ በተጨማሪም በክፍለ ከተማው እየተከናወነ የሚገኘውን የከተማ ግብርና ጎብኝተዋል።

በሔብሮን ዋልታው

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW