ከንቲባዋ ዐርበኝነት አገር መውደድን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የሚገለፅ ነው አሉ

ሚያዝያ 27/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዐርበኝነት አገር መውደድን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የሚገለፅ ዳርቻና ድንበር የሌለው እውነተኛ መገለጫ ነው ሲሉ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለ81ኛው የኢትዮጵያ ዐርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል በስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ዐርበኝነት የታላቅ ስብዕና ክብር መጎናፀፍያ ነው ብለዋል፡፡

ዐርበኝነት ከራስ በላይ ለታላቅ አላማ፣ ለአገርና ለሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት የመቆም የነፃነትና የሉአላዊነት ዘውድ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ከንቲባዋ የማይተካ ህይወታቸውን መስዋዕትነት ከፍለው ለዚህ ቀን ላደረሱን ውድ አባቶቻችንና እናቶቻችን ያላቸውን ታላቅ ክብር እና ምስጋና አቅርበዋል።

የእኛም ትውልድ ከራስ በላይ ለታላቅ አላማ፣ ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ደኅንነትና መበልጸግ በአንድነት በመቆም ዐርበኝነቱን የሚያረጋግጥ ይሆናልም ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።