ከንቲባ አዳነች በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተገነቡ ቤቶችን መርቀው ለአቅመ ደካማ ወገኖች የቁልፍ ርክክብ አደረጉ

ጳጉሜ 1/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት በመከላከያ ኮንስትራክሽን አማካኝነትና በሄይንከን ኢትዮጵያ የተገነቡ ቤቶችን መርቀው ለአቅመ ደካማ ወገኖች የቀልፍ ርክክብ አድርገዋል፡፡

ቀልፉን ባስረከቡበት ወቅት ከንቲባዋ እንደተናገሩት እንደ መንግስት የነደፍነውን ሰው ተኮር ዕቅዳችንን ማዕከል በማድረግ በ2014 ዓ.ም በአጠቃላይ ስምንት ሺሕ ቤቶችን ገንብተን ድጋፍ ለሚሹ አቅመ ደካማ ወገኖች አስረክበናል ብለዋል፡፡

ባለፉት ጊዚያት በዓመት የነበረው ከፍተኛ ቤት የመገንባት አሃዝ ሶስት ሺሕ ነበር ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ከበጎ ፈቃደኞችና ከአገር ወዳድ አካላት ጋር ከተቀናጀን ብዙ መሥራት እንደምንችል የተማርንበትም ምዕራፍ ነው ብለዋል፡፡

በዛሬው ዕለት 952 ቤቶችን ከበጎ ፈቃደኛች ጋር በቅንጅት ግንባታቸውን አጠናቀን ሙሉ በሙሉ ርክክብ እንፈጽማለን ብለው፤ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ ዜጎች በሚፈለገው ልክ ከደገፉን ብዙ በመሥራት በጉብዝናቸው ወራት ለሀገር እጅግ የደከሙ አቅመ ደካማ ወገኖቻችን መደገፍ እንችላለን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል

ከተባበርንና በቅንጅት የየድርሻችንን ኃላፊነት ወስደን ከሰራን ከዚህ በላይ ማሳካት እንደሚቻል የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች አሁን የምንገኝበት ወቅት በጎ ፈቃደኝነት ባህል ልሆን ይገባል ብለዋል

የናንተን እምባ ማበስና የኑሮ ጫና ማቃለል የመንግስታችን ቀዳሚ ኃላፊነት ነው ያሉት ከንቲባዋ በዘላቂነት ተመሣሣይ ችግር ያለባቸውን ወገኖች ለመርዳት ከተማ አስተዳደሩ ከበጎ ፈቃደኞችን ጋር ይሰራል ማለታቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡

የበለጠ እያሰፋን እንድንሰራ የእስካሁኑ የአቅመ ደካማ ወጎኖች ቤት ግንባታ ምሳሌ ሆኖናል ያሉት ከንቲባዋ የምናርፈው በሁሉም ረገድ ሁለንተናዊ ብልጽግናችንን ስናረጋግጥ ብቻ ነው ብለዋል፡፡