ከንቲባ አዳነች በተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በመገኘት በዓሉን በጋራ አሳለፉ

መስከረም 1/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ በቂርቆስ ክ/ከተማ አዲስ በተገነባው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በዓሉን በጋራ አሳልፈዋል፡፡

ከንቲባዋ ከቢኬጂ ፋውንዴሽን ጋር በመሆን ነው በዓሉን ከምገባ ማዕከሉ ተጠቃሚዎች ጋር ያሳለፉት።

በዚሁ ወቅት ከንቲባ አዳነች፤ “ዛሬ አዲሱ አመት ገና ሲጀምር ከእናንተ ጋር ማዕድ በመቋደስ ለእናንተ ፍቅር በመስጠት ማሳለፍ መታደል ነው፤ ትልቅ ደስታንም የሚሰጥ ነው” ብለዋል፡፡

ወገን ለወገን የመተሳሰብ እሴታችን ማደግ እና ለትውልድ መተላለፍ ያለበት ነውም ብለዋል ፡፡

የቢኬጂ ፋውንዴሽን ባለቤት በላይነህ ክንዴ በበኩላቸው፥ ድርጅታቸው በማህበራዊ ግልጋሎት፣ በትምህርት በጤናና ስፖርት የተለያየ ሃገራዊ ጉዳዮች እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ይህም የምገባ ማዕከል በ20 ሚሊየን ብር ተገንብቶ ወደ ተግባር መግባቱን አስታውሰዋል፡፡

አሁንም በምገባ ማዕከሉ ሴቶችን አደራጅቶ ወደ ስራ በማስገባት የ800 ሺህ ብር እቃ ምገባውን የሚያከናውኑበት እንዲሁም ለስራ ማስጀመርያ የ200 ሺሕ ብር ድጋፍ እንደሚያስረክቡም ገልፀዋል፡፡

የቂርቆስ ቢኬጂ ፋውንዴሽን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በመመገብ ላይ እንደሚገኝ መገለፁን የከንቲባ ፅ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡