ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን በማዘመን ሕገ ወጥነትን መከላከል ይገባል አሉ

ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ጥር 9/2014 (ዋልታ) ለከተማ ቤቶች አስተዳደር ሥርዓት የሚያገለግል ሶፍትዌር በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ለምቶ በይፋ የሥራ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሂዷል።

በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የለውጡ አመራር ወደ ሥራ ሲገባ ተግባራዊ ሊያደርጋቸው ቃል ከገባባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ አሰራሮችን ቀልጣፋና ግልፅ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለማዘመን ዛሬ ተግባራዊ የሆነው ሶፍትዌርም የአሰራር ለውጡ አንድ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት በአግባቡ ለመስጠት ሶፍትዌሩ ላይ የሚገቡ መረጃዎችን ከመሰብሰብ ጀምሮ አጠቃላይ ተግባራዊነቱ ላይ ትኩረት በመስጠት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

ፍትሃዊነትን ለማስፈንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ለትክክለኛ መረጃ አያያዝ የሚያገለግሉ ሶፍትዌሮችን መጠቀም ጥቅሙ የጎላ እንደሆነም አንስተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በከተማው የሚገኙ ቤቶችን በዚህ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሶፍትዌር አማካኝነት በማስተዳደር ሌብነትና ሕገ ወጥነት እንዳይስፋፋ ይሰራል ማለታቸውን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሶፍትዌሩ የቀበሌ ቤቶች፣ ኮንዶምንየሞች፣ የማኅበራት ቤቶች፣ ህንፃዎች እና ክፍት ቦታዎች ያሉበትን ቦታ በመመዝገብ በመረጃ ስለሚይዝ የፋይል መጥፋትና መሰል ችግሮችን ይቀርፋል ተብሏል።