ከአማራ ክልል 3 ቦታዎች ተነስተው ሲዘዋወሩ የነበሩ ሕገወጥ መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የካቲት 8/2014 (ዋልታ) መነሻቸውን ከአማራ ክልል 3 የተለያዩ አካባቢዎች ያደረጉና በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ 19 ሺሕ 447 ጥይቶች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል ከአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ከአማራ እና ከኦሮሚያ ክልሎች ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር በቅንጅት በተሰራው ሥራ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ እንዳመለከተው መነሻውን ከአማራ ክልል ባሕርዳር ከተማ ያደረገ አንድ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪ ግለሰብ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 A 79848 አ.አ በሆነ ፒካፕ ተሽከርካሪ 4 ሺሕ 847 የክላሽ ጥይት ጭኖ መዳረሻውን አዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ በመጓዝ ላይ እያለ በተደረገበት ክትትል በቁጥጥር ስር ውሏል።

በተመሳሳይ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ3 አ.ማ 20386 በሆነ ፒካፕ ተሽከርካሪ ከአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ ተጭኖ ወደ ጎንደር እንዲደርስ ታቅዶ የነበረ 14 ሺሕ 500 የክላሽ ጥይት በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

መነሻውን አማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ ያደረገ አንድ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ግለሰብ በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በእህል ውስጥ 100 የብሬን ጥይት እና 3 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ደብቆ በመጫን ለማሳለፍ ያደረገው ሙከራም በፀጥታ ኃይሎች መክሸፉን ለዋልታ የደረሰው መረጃ አመልክቷል፡፡