ሰኔ 7/2014 (ዋልታ) ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በአስር ወራት 418 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በ2014 በጀት ዓመት በአስር ወራት ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ 498 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቀዶ 418 ሚሊየን ዶላር ገቢ በማስመዝገብ የዕቅዱን 84 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ተገልጿል።
የተገኘው ገቢ ካለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ102 ሚሊየን ዶላር ጭማሬ አሳይቷል።
ገቢው ወደ ውጭ ከተላከ 146 ሺሕ 342 ቶን ምርት የተገኘ ሲሆን የተላከው የምርት መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ17 ሺሕ 634 ቶን ጭማሬ አስመዝግቧል፡፡
ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት 153 ሚሊየን ዶላር፣ ምግብና መጠጥ 93 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች 33 ሚሊየን ዶላር፣ ኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች 22 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር፣ ማምረቻው ዘርፍ፣ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ 16 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር እና ሥጋና ወተት አፈፃፀም 98 ሚሊየን ዶላር ድርሻ አላቸው።
ከአጎዋ የገበያ እድል መቋረጥ ጋር ተያይዞ አምራቾች ያጡትን የገበያ እድል ሊተኩ የሚችሉ አማራጭ ገበያ መዳረሻዎችን ለመለየት ጥናት የማካሄድ ሥራዎች ሲከናወኑ እንደነበር የሚኒስቴሩ መረጃ ጠቁሟል፡፡
በሌላ ዜና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ከኢኳቶሪያል ጊኒ የማዕድን ኢንዱስትሪ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ጋር በሀገራቱ መካከል ያለውን የአምራች ኢንዱስትሪ ትስስር ለማጠናከርና በቀጣይም ዘርፉን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡