ከአንድ ሺሕ በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮች የቡና ላኪነት ፈቃድ አገኙ

ታኅሣሥ 19/2015 (ዋልታ) ባለፉት ሦስት ዓመታት ከአንድ ሺሕ በላይ አርሶ አደሮች የቡና ላኪነት ፈቃድ ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ሻፊ ኡመር ባለፉት አራት ዓመታት የሪፎርም ስራዎችን ሲከናውን መቆቱን ገልጸው የቡና ምርት ጥራትን ማስጠበቅ፣ የግብይት ስርዓቱን ማዘመንና በምርቱ ላይ እሴት በመጨመር ምርታማነቱን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሪፎርሙ በቡና ግብይት ላይ ከፍተኛ እድገት በማምጣት ባለፈው በጀት ዓመት 302 ሺሕ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡

የሪፎርም ስራዎች መተግበር ከጀመሩ ወዲህ ባሉ አራት ዓመታት ወደ ውጭ የተላከ የቡና ምርት በ104 ሺሕ ቶን እድገት ማስመዝገቡንም ነው የገለጹት፡፡

ባለስልጣኑ የዓለም የቡና ገበያ ተለዋዋጭነትን መሰረት በማድረግ ተጨማሪ የገበያ መዳረሻዎችን የማፈላለጉን ስራ በትኩረት እያከናወነ መሆኑን ገልጸው እንደ ኤዥያ ባሉ አካባቢዎች አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

የቡና ላኪነት ፈቃድ ካገኙ ከአንድ ሺሕ በላይ አርሶ አደሮች መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑ ቡናቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡም ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮ በጀት ዓመት 360 ሺሕ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡