ጳጉሜ 3/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኡራኤል ወደ ወሎ ሰፈር የሚወስደውንና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተገነባውን አዲስ መንገድ የሰላም ጎዳና ብሎ መሰየሙ ተገለጸ፡፡
በሰላም ጎዳና ስያሜ መርኃ ግብር ላይ የአስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለምን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ከንቲባ በሰላም ጎዳና ስያሜ መርኃ ግብር ላይ በቅርብም በሩቅም ለወዳጆቻችንም ሆነ ለሌሎች የምናስተላልፈው መልዕክት ዋናው ዛሬ መንገድ የመሰየማችን ዓላማ አጠቃላይ “የኢትዮጵያ ጉዞ የሰላም መሆኑን ለተቀረው ዓለም ማመላከት ነው” ብለዋል።
ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያ አስቀድማ ለሰላም ዘርግታው የነበረው እጇ አለመታጠፉን ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር አብረው ለሚወጉን አካላት ሁሉ ለማሳወቅ እንወዳለን ብለዋል ከንቲባዋ፡፡
የሰላም ሚንስትር ብናልፍ አንዷለሞ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ለሰላም ለሰጡት የላቀ ስፍራና ለዚህ ጎዳና ሲያሜ ሊመሰገኑ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለሰላም አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍለን ሁላችንም በአንድነት የአገራችንን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የሚጠበቅብን በመሆኑ በሁሉም ረገድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የዕለት ተግባራቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲያከናውኑ ሰላም ቁልፍ በመሆኑ ለሰላም መረጋገጥ በየደረጃው አቅማችን በሚፈቅደው ሁሉ በነፍስ ወከፍ ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል ማለታቸውን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
በመንገድ ስያሜ መርኃ ግብር ላይ የተገኙ የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች ኢትዮጵያ ወጣቶች ሰርተው የሚለወጡባትና አረጋዊያን የሚጦሩበት አገር እንድትሆን ከሁሉም በላቀ ለአገር ብልጽግና መጸለይን፣ የሕዝብ ለሕዝብ ወንድማማችነትና ትስስር እንዲጎለብት መስራትን ጨምሮ በላቀ ግብረገብነት ወጣቶች የዕድሜ ታላላቆቻቸውን የሚያከብሩ፣ በአንድነት የሚያምኑና አገራቸውን የሚወዱ እንዲሆኑ ሃይማኖቶች ማስተማርና መምከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!