ከኤሌክትሪክ አውታር ውጪ ኢነርጂን ተደራሽ ማድረግ

ጳጉሜ 03/2013 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ አውታር ውጪ ኢነርጂ ተደራሽ ለማድረግ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት አብረው ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ይፋ ሆነ፡፡

በ2017 በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በእንግሊዝ መንግሥት መካከል ተፈርሞ የነበረው ኢነርጂ ኮምፓክት የተሰኘውን መርኃግብር ከሀገር አቀፍ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራምና ሌሎች ፖሊሲዎች ጋር ተጣጥሞ የተዘጋጀው አዲስ ሰነድ ይፋ መሆኑን በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ፖሊሲና የፖወር ሴክተር አማካሪ አቶ ጎሳዬ መንግሥቴ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በሶላር ኢነርጂ ዙሪያ የሚሠሩ ተዋንያንን፣ ገንዘብ የሚለግሱ አካላትን፣ የግሉን ዘርፍ፣ የሶላር ኢነርጂ ማህበራትና የመንግሥት ተቋማትን አንድ ላይ በማምጣት በዘርፉ የቴክኖሎጂውን ጥራትና ደራጃ፣ የቀረጥ ማበረታቻን እና የዲጂታል ክፍያ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይም ምክክር ተደርጓል ተብሏል፡፡

የአፍሪካ ክሊን ኢነርጂ ካንትሪ ዳይሬክተር ኤደን ፈንታ በበኩላቸው፣ ዘርፉ ላይ ያሉ ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት ኢትዮጵያ በ2025 ያስቀመጠችውን ኢላማ ማሳካት እንዲቻል በጋራ መሥራት የሚቻልበትን ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ዘርፉ ላይ ሥራዎችን የሚሠሩ አካላት የመንግሥት ፖሊሲና ፕላንን ታሳቢ በማድረግና በተናበበ መንገድ ሥራዎችን ለመሥራት እንዲሁም በዘርፉ ባሉችግሮች ዙሪያ በመምከር መፍትሔዎችን ያመጣ ውይይት ነው ብለዋል፡፡

በውይይቱ የሚኒስቴሩ እና ተጠሪ ተቋማት ባለሙያዎች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍ ማኅበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡