ከክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን ክረምት ከመግባቱ በፊት ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ እንደሚሰራ ተገለጸ

ሚያዝያ 28/2013 (ዋልታ) – ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን ክረምት ከመግባቱ በፊት ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ እንደሚሰራ ተገለጸ።

በክልሉ የሰብአዊ ድጋፍ በተጠናከረ መንገድ እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴርና የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በጋራ በሰጡት መግለጫ ገልጿል።

በመግለጫው በመጀመሪያው ዙር ለ4.5 ሚሊየን ዜጎች ድጋፍ የደረሰ ሲሆን፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ለ2.7 ሚሊየን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደተደረገ ተጠቁሟል።

በዚህም 3.7 ቢሊየን ብር ወጭ የተደረገ ሲሆን፣ 70 በመቶው በመንግስት እንደተሸፈነ እና 30 በመቶ በአጋር ድርጅቶች ተሸፍኗል ነው የተባለው።

መንግስት የ3ኛው ዙር ሰብአዊ ድጋፍ ላይ የአሰራር ሃደት ይቀይራል የተባለ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ከነበረው መንግስትና ሁለት ሰባአዊ ድጋፍ አድራጊ አጋር አካለት በተጨማሪ አራት አጋር አካለት ተጨምረው የሰብአዊ ድጋፍ እንደሚደረግ ተገልጿል።

በትግራይ ክልል ከሚገኙ 92 ወረዳዎች ውስጥ 86 በመቶን አጋር አካላት የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያደርጉና ቀሪ 14 በመቶ የሚሆነው በመንግስት እንዲሸፈን እየተሰራ እንደሆነና ይህም መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ያሳያል ተብሏል።

ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው በ12 ካምፖች የሚገኙ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን ተፈናቃዮችን ክረምቱ ሳይገባ ወደ ቀያቸው በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረት የመመለስ ስራ እንደሚሰራም በመግለጫው ተጠቁሟል።

በትግራይ ክልል ወደ ቀያቸው የሚመለሱ ዜጎች በ2014 ዓ.ም  ተረጂ እናዳይሆኑና የግብርና ምርት እንዲያመርቱ 126 ሺህ 614 ኩንታል ማዳበሪያ እና 5 ሺህ 580 ኩንታል ምርጥ ዘር ወደብ ላይ እንደደረሰም ተመላክቷል።

በአሁኑ ሰዓት ለሰብአዊ ድጋፍም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ወደ ትግራይ ክልል መጓዝ የሚፈልጉ አካላትን በቀላሉ መንቀሳቀስ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱም ተገልጿል።

በመላው ሀገሪቱ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ 2.1 ሚሊየን ዜጎች ተፈናቅለዋል የተባለ ሲሆን፣ ክረምቱ ሳይገባ መደ ቀያቸው ለመመለስ ይሰራል ተብሏል፡፡

በአጣዬና አካባቢው በደረሰው ጥቃት መጀመሪያ ላይ ከአማራ ክልል ወደ ፌደራል ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የደረሰው 50 ሺህ ተፈናቃይ ነው ስለተባለ መረጃው በደረሰ ሰዓት እርዳታ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡ ሆኖም አሁን ላይ 250 ሺህ ተፈናቃይ እንዳለ መረጃው በመድረሱ ስብአዊ ድጋፍ ለማድረስ እየተሰራ እንደሆነ በመግለጫ ተገልጿል።

(በምንይሉ ደስይበለው)