ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የተወጣጡ ወጣቶች በባሕርዳር የልምድ ልውውጥ እያደረጉ ነው

የካቲት 15/2014 (ዋልታ) ከ300 በላይ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ወጣቶች መላው የአማራ ክልል ከተሞችንና ዞኖችን በመጎብኘት የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ባሕርዳር ከተማ ገብተዋል።

ወጣቶቹ ጦርነቱ በተካሄደባቸው ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የደረሰውን ውድመት ከመጎብኘትም ባሻገር ከተለያዩ አካላት ጋር ይወያያሉ ተብሏል፡፡

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) የአማራን ባህል፣ እምነትና ቋንቋ ባላገናዘበ መልኩ በወቅቱ የነበረው ሥርዓት በኃይል በመጫን እና በማስገደድ የወልቃይት ሴቲት ሁመራ ዞን ከወንድሙ የአማራ ሕዝብ ተነጥሎ እንዲቆይ ተገዶ ነበር ብለዋል።

ይህ ትግል ሲጀምር ሁሉም ከዳር እስከ ዳር የተነሳ ቢሆንም ባሕርዳር ላይ “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ!” በማለት ከወልቃይት ሕዝብ ጎን በመቆም እስከ ህይወት መስዋእትነት የተከፈለ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከ56 በላይ የባሕርዳር ከተማ ወጣቶች ለወንድም የወልቃይት ሕዝብ ነጻነት ህይወታቸውን መገበራቸውን አስታውሰው የጀመርነውን ትግል ፍጻሜ ለማድረስ በጋራ የሚከፈለውን ለመክፈል ከጎናችሁ ነን ብለዋል።

የአማራ ከልል ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጋሻው ተቀባ በበኩላቸው ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት ማንነትን መሰረት ያደረገ ግፍ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ ላይ ሲደርስ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው በበኩላቸው የአማራ ሕዝብ ብዙ ሴራና ደባ የደረሰበት እና የተተበተበበት ዋነኛ መነሻው የወልቃይት ጠገዴን መሬት በመጠቀም ታላቋን ትግራይ ለመገንባት ያለመ ነበር ብለዋል።

በዚህም የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ እልፍ ግፎችን እንዳሳለፈ ገልጸው ወጣቶች በጅምላ እንዲቀበ፣፤ በቋንቋቸው እንዳይማሩና ባህላችን በግድ በሌላ ማንነት እንዲጫን ከማድረግ በላይ በልማት ተጠቃሚ እንዳይሆን ሲያደርግ እንደቆየ ገልጸዋል።

በቀጣይም ትግላችን ያልተጠናቀቀ በመሆኑ አማራ እንደ አማራነቱ አንድነቱን ማጠናከርና መደማመጥ እንዳለበት መልዕክት ማስተላለፋቸውን የባሕር ዳር ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።