ከውጭ የሚገባውን የሩዝ ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት መሰራት እንደሚገባ ተጠቆመ

ጥቅምት 17/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ለሩዝ ምርት ምቹ የሆነ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ቢኖርም እየለማ የሚገኘው 2 በመቶው ብቻ ነው ተባለ፡፡
በዚህም 80 በመቶ የሩዝ ፍላጎቷን ከውጭ በማስገባት ለመሸፈን ተገዳለች፡፡
በመሆኑም ከውጭ የሚገባውን በአገር ውስጥ ለመተካት መስራት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
ችግሩን ተረድቼ ወደ ሥራ ገብቻለሁ ያለው የደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ፎገራ ብሔራዊ የሩዝ ምርምርና ስልጠና ማዕከል 8 የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎችን በማቅረብ ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ እንደሆነ ገልጿል፡፡
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ሸዋዬ አበራ ማዕከሉ በሩዝ ላይ ምርምር ከጀመረበት 2012 ወዲህ ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የማዕከሉ የግብርና ኤክስቴንሽንና ኮሙዩኒኬሽን ምርምር ክፍል አስተባባሪና ተመራማሪው ምስጋናው አንተነህ አካባቢው ሩዝን ለማምረት ካለው አቅም አንፃር እንዳልተሰራበት ጠቅሰዋል፡፡
በትዕግስት ዘላለም (ከባሕር ዳር)