ከዛሬ ጀምሮ የሲሚንቶ ግብዓትና ምርት ስርጭትን በሚያስተጓጉሉ ህገ-ወጦች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የኦሮሚያ ክልል አስታወቀ

ግንቦት 24/2014 (ዋልታ) የሲሚንቶ ግብዓትና ምርት ስርጭትን በሚያስተጓጉሉ ህገ-ወጦች ላይ አስፈላጊን እርምጃ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚወስድ የኦሮሚያ ክልል አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዱና የመዓድንና ኢነርጂ ሚኒስትር ታከለ ኡማ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዱ በመግለጫቸው፤ በክልሉ በሲሚንቶ ምርት ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የሚያስችል እርምጃ ክልሉ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።

በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች በሚገኙ  ያልተገባ ክፍያ በመጠየቅ የግብዓትና ምርት ስርጭት ላይ እንቅፋት የሆኑ ኬላዎችን በማንሳት ግብዓቱ በቀጥታ ወደ ፋብሪካዎች የሚደርስበት አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

አክለውም ምርቱ ከፋብሪካዎች በ400 ብር እና በ500 ብር የሚወጣ ቢሆንም በርካታ ደላሎች በመሀል የምርቱን ዋጋ እስከ 1 ሺሕ ብር ከፍ እንዲል ማድረጋቸው በመግለጫው ተነስቷል።

በመሆኑም ክፍተቶችን በመፈተሽ ህጋዊ ማኅበራትን በማደራጀት የምርት ስርጭቱ በቀጥታ ወደ ተጠቃሚው

የሚደርስበትን አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል።

ከአምራች እንደስትሪዎች ጋር በተገናኘ የሚነሱ የፀጥታና የግብዓት ችግሮች ለመቅረፍ ክልሉ ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑና ችግሩንም ለመቅረፍ ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመዓድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ እንዲህ አይነቱ እርምጃ የምርትና ግብዓት ሳይቆራረጥ ለተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርስ ያስችላል ብለዋል።

ሌሎች ክልሎችም እንዲህ አይነቱን አሰራር እንዲከተሉ እድል የሚፈጥር እንደሆነ የገለፁ ሲሆን የክልሉ እርምጃ የሲሚንቶ ምርት እጥረት ለማሳደግ የራሱ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።

ሚድሮክ፣ ዳንጎቴ፣ ደርባን፣ ዳንጎቴ፣  ሙገር፣ ደርባ፣ ሀበሻና ሌሎችም በክልሉ ሲሚንቶ አምራች የሆኑ የግል አልሚዎች  ጋር በዚህ ደረጃ በጋራ ለመስራት ጋር ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑም ተገልጿል።

በደረሰ አማረ