ከዳውሮ ዞን ለመከላከያ ሰራዊት የተደረገ ድጋፍ ለመከላከያ ሰራዊት የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ጋር ርክክብ ተደረገ

ነሀሴ 21/2013 (ዋልታ) – ከዳውሮ ዞን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የተደረገ ከ31 ሚልሊየን ብር በላይ የሚገመት  የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ ለመከላከያ ሰራዊት የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ጋር ርክክብ ተደረገ።

የዳውሮ ህዝብ የአሸባሪዎችን ሴራ ለማክሸፍ ግንባር ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የተደረገ ከ31 ሚልዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ  ቢሾፍቱ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የሀብት አሰባሰብ ኮሚቴ ገቢ ተደርጓል።

በርክክብ መርሀግብሩ ላይ የተገኙ የዳውሮ ዞን የብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ መንግስቱ መኩሪያ መላው የዳውሮ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

አቶ መንግስቱ አክለውም ከመላው የዳውሮ ህዝብ ከህዝብ የተሰበሰበ 169 ሰንጋ፣ በርካታ በግና ፍየል፣ 300 ኪ.ግ ቅቤ፣ 53 ኩንታል ደረቅ ስንቅና 2 ሚሊየን ብር በጥረ ገንዘብ በአጠቃላይ ከ31 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።

አሁን ኢትዮጵያን ለማዳን ግንባር ለተሰለፉ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከመላው የዳውሮ ህዝብ የተደረገው ድጋፍ ከዕቅድ በላይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መንግስት፣ የአሸባሪው ሀይል ግብአተ መሬት እስኪፈጸም ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አሳውቀዋል።

በመርሃግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ክልል በም/ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ መላው የክልሉ ህዝብና መንግስት ከዳር እስከ ዳር በመረባረብ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያደረገው ድጋፍ የሚያኮራ መሆኑን ገልፀው፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እስከ ግንባር ድረስ በመሄድ ለሰራዊቱ ሞራል በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

አቶ ተስፋዬ ይገዙ አያይዘውም መላው የክልሉ ህዝብና መንግስት ባደረገው ርብርብ 2087 ሰንጋ፣ 580 በግና ፍየል እንዲሁም 113 ሚሊየን ብር ጥረ ገንዘብ ገቢ መደረጉንና ተጨማሪ 200 ሚሊየን ጥረ ገንዝብ ገቢ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል ።

የደቡብ ክልል ህዝብ ለሀገር ክብር እጅግ የተለየ ድጋፍ በማድረግ የክልሉ ህዝብ  አንድ አይደሉም ለሚሉ አካላት አንድነታቸውን በተግባር አሳይተዋል ያሉት የመከላከያ ሰራዊት የሀብት አሰባሰብ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄነራል አስረስ አየለ ናቸው።

ከዳውሮ ዞን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የተደረገውን ድጋፍ ለማስረከብ የዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ መንግስቱ መኩሪያ፣ የፓርቲው የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ የዞኑ የሀብት አሰባሰብ ኮሚቴ ም/ሰብሳብ አቶ አክልሉ ለማን ጨምሮ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶችና የወጣቶች ተወካዮች፣ በክብር ተሰናባች መከላከያ ሰራዊት አባላት ተወካዮች፣ የዞኑ ፖሊስ አመራርና የሚዲያ አካላት መገኘታቸውን ከዞኑ የመን/ኮ/ጉ/መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።