ከዳያስፖራው ወደ አገር ቤት የሚላከውን ገንዘብ ለማሳደግ ቀልጣፋ የፋይናንስ ሥርዓት እንደሚያስፈልገው ተጠቆመ

የምጣኔሃብት ምሁሩ ሙላቱ ፍቃዱ (ፕ/ር)

ታኅሣሥ 14/2014 (ዋልታ) ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት የሚልከውን ገንዘብ ለማሳደግ መንግሥት ቀልጣፋ የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት ይኖርበታል ሲሉ የምጣኔሃብት ምሁሩ ሙላቱ ፍቃዱ (ፕ/ር) ገለጹ።

ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት የሚልከው ገንዘብ ሕጋዊ ሥርዓትን መከተል እንዳለበት የገለጹት በደቡብ አፍሪካ የሱዋኔ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ሙላቱ ፍቃዱ (ፕ/ር)  ከውጭ የሚላከው ገንዘብ (ሬሚታንስ) የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ዳያስፖራው ይህን በመገንዘብ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

በእስያ የሚገኙ አገራት ከአጠቃላይ ምርታቸው ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ከውጭ አገር በሚገባ ገንዘብ እንደሚያገኙ ለአብነት የጠቀሱት ምሁሩ ከሬሚታንስ የሚገኝ ገቢ ለኢትዮጵያም እንደተጨማሪ የሃብት ማሰባሰቢያ ተደርጎ መወሰድ አለበት፤ መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም ዳያስፖራው ገንዘቡን ያለምንም ችግርና ቅድመ ሁኔታ ወደ አገር ቤት እንዲልክ ለማድረግ ቀልጣፋ የገንዘብ ፍሰት መኖር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል የአገሪቷን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት በቀጣናው ከሚገኙ ጎረቤት አገራት ጋር ሁለንተናዊ ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በማንኛውም የልማትና የእድገት እንቅስቃሴዎች ከአፍሪካ በተለይም ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር ያስፈልጋልም ብለዋል።

ዳያስፖራው ባለፉት ሶስት ዓመታት በአማካይ 3 ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ ወደ አገር ውስጥ መላኩን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።