ከፍተኛ አመራሮች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመከላከያ ሰራዊት ለመለገስ ቃል ገቡ

ጳጉሜ 1/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ለመለገስ ቃል ገብተዋል።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሎጀስቲክ ድጋፍ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በመድረኩ ላይም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሚስራ አብደላ እንዳሉት አሸባሪው ህውሃት የተሰጠውን ተደጋጋሚ የሰላም አማራጭ በመግፋት በሀገሪቱ ላይ ጦርነት ከፍቷል።
በሀገር ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመመከት እየተዋደቀ ለሚገኘው የፀጥታ ሀይል የሎጀስቲክስና የሀብት አሰባሰብ ኮሜቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመው በክልሉ በአጠቃላይ ከ33 ሚሊየን ብር በላይ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችም የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ለመለገስ ቃል መግባታቸውን ገልፀዋል።
የሀገር ሰላምና ሉአላዊነት የሚጠበቀው መላው ህዝብ በሚያደርገው አስተዋጽኦ መሆኑን ጠቁመው የሽብር ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት በተለይም ባለሀብቱ፣ ነጋዴውና ሌላው የማህበረሰብ ክፍል በሀብት ማሰባሰቡ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙ የክልሉ አመራሮችም አሸባሪው ህውሃት የከፈተውን ጦርነት ለመመከት የአንድ ወር ደሞዝ ከመለገስ ባለፈ የህይወት መስዋዕትነት እስከ መክፈል የሚደርስ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር ቅርንጫፍ)