ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የወጪ ቅነሳን ተግባራዊ እንዲያደረጉ ማሳሰቢያ ተሰጠ

ሚያዝያ 26/2014 (ዋልታ) ገንዘብ ሚኒሰቴር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የወጪ ቅነሳ ተግባራዊ እንዲያደረጉ አሳሰበ፡፡
ለሁለተኛ ቀን የዘለቀው የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የ2015 አመት በጀት ሲገመገም የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የወጪ ቅነሳ ጉዳይ የ2015 በጀት አመት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በበጀት አመቱ አዳዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዳማይኖሩና ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸው ንብረት ታውቆ በአንድ የመረጃ ቋጥ ውስጥ እንዲካተት ተደርጎ የገንዘብ ሚኒሰቴር ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር በጋራ በመሆን በቀጣይ የክትትልና የቁጥጥር ስርዓት እንደሚዘረጉ አስረድተዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒሰቴር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝም (ዶ/ር) በበኩላቸው የካፒታል ፕሮጅክቶች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል የተለያዩ ሥራዎችን ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውና የፋይናንስ ስርዓቱን በህጉ መሰረት ተግባራዊ ባላደረጉ የተቋማት ኃላፊዎችና ባለሞያዎች ላይ እርምጃ መወሰድ መጀመሩንም አመልክተዋል፡፡
በበጀት ስሚ ፕሮግራሙ ላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በሚኒስቴሩ ከተቀመጠላቸው የበጀት ጣሪያ በላይ ያቀረቡ ሲሆን በምክንያትነት ካቀረቡት ጉዳዮች ውስጥ የተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ፣ የምግብ፣ የሌሎች ሸቀጦችና የመድሐኒት ዋጋ መጨመር እንዲሁም ያልተጠናቀቁ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ሥራ መኖራቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የተማሪዎች የምግብ አቅርቦትና ሌሎች የምግብ ሸቀጦች በአግባቡ መተመን እንዲቻል ዝርዝር ጥናት በባለሞያዎች ተጠንቶ ለውሳኔ ለበላይ አካል እንዲቀርብ አቅጣጫ መቀመጡን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡