ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን እና የሚዲያ ኃላፊዎችን ያካተተ የልዑካን ቡድን በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው የካብሳት ኤክስፖ ላይ እየተሳተፈ ነው

ግንቦት 13/2016 (አዲስ ዋልታ) ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን እና የሚዲያ ኃላፊዎችን ያካተተ የልዑካን ቡድን በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው የካብሳት ኤክስፖ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

በኤክስፖው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) እና ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰላማዊት ካሳ፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና፣ የዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ መሀመድ ሀሰንን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡

“Cable, Satellite, Broadcast, and Telecommunications,” ወይም ካብሳት ኤክስፖ ስሙ ራሱ እንደሚያመለክተው፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአፍሪካ እና በደቡብ እስያ ላሉ፣ የሳተላይት እና ብሮድካስት ኢንደስትሪዎች፣ በየአመቱ የሚዘጋጅ የንግድ ትርኢት ነው፡፡

ትርኢቱ፣ በአይነቱ፣ ከአለም 3ኛው እና ዘንድሮም ለ30ኛ ጊዜ ነው እየተዘጋጀ የሚገኘው፡፡ ትርኢቱ ላይ፣ የሳተላይት፣ የብሮድካስት ቴክኖሎጂ፣ የኬብል ኔትወርክ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን መፍትሄዎች እና የመሳሰሉት ምርቶች እና አገልግሎቶች፣ ለፈላጊዎች ይቀርባሉ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (በስተቀኝ) እና የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋዜጠኛ መሀመድ ሀሰን (በስተግራ) እና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (መሀል)

የኢንዱስትሪው ኤክስፐርቶች፣ ስለ አዳዲሶቹ ፈጠራዎች እና ቴክኖሎጂዎች፣ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዚሁ ኤክስፖ ላይ በኬብል፣ በሳተላይት፣ በብሮድካስቲንግ እና ቴሌኮሙኒኬሽን መስክ የሚገኙ፣ አምራቾች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎች በአንድ ቦታ እንደመገኘታቸው ፣ ስለ ኢንደስትሪው እድገት፣ ስለ ትብብር፣ ስለ ኔትወርክ መፍጠር እና የመሳለውን ይመክራሉ፡፡

የመካከለኛው ምስራቅ፣ የሚዲያ እና የመዝናኛው ገበያ፣ በ2024 42.72 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ በ2029 ይህ አሀዝ፣ 66.99 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚደርስ ተተንብይዋል፡፡

በዘንድሮው የንግድ ትርኢት ላይ፣ ከ120 አገሮች የተውጣጡ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል ፣ የዚህ አመቱ ትርኢት ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሀሙስ ባሉት ቀናት ይካሄዳል፡፡