ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

ግንቦት 30/2014 (ዋልታ) 110 ሚሊዮን 66 ሺሕ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በተደረገ ክትትል 87 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 22 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ አስታውቋል፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሞያሌ፣ ጅግጅጋ እና ድሬዳዋ  ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተላቸው 25 ነጥብ 1 ሚሊዮን፣ 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን እና 12 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን ተይዞባቸዋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣  ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡