ከ2 ሺሕ በላይ የመዲናዋ ወጣቶች በወቅታዊ ጉዳይ እየመከሩ ነው

ኅዳር 4/2014 (ዋልታ) “በመረረ ትግላችን ጣፋጭ ድል እናጣጥማለን” በሚል መሪ ሃሳብ ከ2 ሺሕ በላይ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ እየመከሩ ነው።
የአከባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ እየጠበቁ የሚገኙ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተወጣጡ ከ2 ሺሕ በላይ ወጣቶች በመድረኩ ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ኃላፊ አብርሀም ታደሰ ባለፉት ጥቂት ወራት ከ27 ሺሕ 540 በላይ ወጣቶች አካባቢያቸውን ከፀረ ሰላም ኃይሎች ለመታደግ ሰልጥነው ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር የአሸባሪውን ሕወሓት ቡድን እና እኩይ አገር የማፍረስ ሴራውን ለማክሸፍ የአዲስ አበባ ወጣቶች ግንባር ድረስ በመዝመት የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።
በደልን፣ ጭቆናን እና መገፋትን እምቢ የሚለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት ለመከላከል እንዲሁም በማኅበራዊ ትስስር ገፆች እየተሰራጨ የሚገኘውን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በመቋቋም እውነት ከፍ ብላ እንድትወጣ ለማድረግ ወጣቱ በአንድነት መቆም ይኖርበታል ተብሏል።
በውይይት መድረኩ የልማት ሥራዎች እንዲቀጥሉ በተቀናጀ መልኩ በመስራት ወጣቶች የአገር ደጀን መሆናቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋልም ተብሏል።