ነሀሴ 17/2013 (ዋልታ) – ባሳለፍነው ሳምንት ከ21 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
ከዚህ ውስጥ 18 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች በ11 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ሞያሌ፣ ሀዋሳ እና አዋሽ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣በፌደራል ፖሊስ፣ በመከላከያ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ እና በጥቆማ የተያዙ መሆናቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።
ከተያዙት እቃዎች ውስጥ ምግብ ነክ ቁሳቁስ ፣ አልሳባት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ መድሀኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎችና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡