ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ሚያዚያ 18/2013 (ዋልታ) – ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ልዩ ልዩ የገቢና የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ከሚያዚያ 7 እስከ 14/2013 ባለው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ባደረገው የኮንትሮባንድ ቁጥጥር ስራ ግምታዊ ዋጋቸው 30 ሚሊዮን 227 ሺ 549 ብር የሚያወጡ ልዩ ልዩ የገቢና ወጪ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ነው የገለጸው፡፡

በገቢ ኮንትሮባንድ 25 ሚሊዮን 865 ሺ 213 ብር የሚያወጡ የተለያዩ አልባሳት፣ኤሌክትሮኒክስ ፣ መድሃኒት፣ምግብ ነክ ሸቀጣሸቀጥ ፣ ኮስሞቲክስ፣መለዋወጫ፣ሲጋራና የተለያዩ የጦር መሳሪያ ተይዘዋል፡፡

በወጪ ኮንትሮባንድነት የተያዙት ደግሞ 4 ሚሊዮን 362 ሺ 336 ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የአሜሪካ ዶላርን ጨምሮ የልዩ ልዩ ሀገራት የመገበያያ ገንዘብ፣ ሀሺሽና ቡና በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተጠቅሷል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በመከላከያ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በደፈጣ መያዛቸው ተጠቁሟል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ሲያንቀሳቅሱ የነበሩ 21 ተሸከርካሪዎችን ጨምሮ 2 ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ይገኛል ተብሏል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ኮንትሮባንድን በመከላከሉ በኩል አጋዥና ተባባሪ በመሆን ለሀገራቸው አለኝታነታቸውን በተግባር ማሳየት እንዳለባቸው ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡