ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ኅዳር 6/2014 (ዋልታ) ባሳለፍነው ሳምንት ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጭ ኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን እንደገለጸው ባሳለፍነው ሳምንት ባደረገው ክትትል ከ26 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በላይ የገቢ እንዲሁም ከ3 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የወጭ ኮንትሮባንድ እቃዎች በ11 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረገው የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በብርበራና በጥቆማ የተያዙ መሆኑን የኮሚሽኑ መረጃ አመልክቷል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ አደንዛዥ እፆች እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡