ከ30 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ይዞ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያዘዋውር የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

የአዲስ አበባ ፖሊስ

ሐምሌ 16/2013 (ዋልታ) – ከ30 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ይዞ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያዘዋውር የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት መሆኑ ተገለጸ፡፡

ተጠርጣሪው የተያዘው በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው 22 አንድ ተብሎ በሚጠራው ባቡር ጣቢያ ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

ግለሰቡ በወቅቱ 30 ሺህ 204 የአሜሪካ ዶላር ይዞ ባቡር ሊሳፈር ሲል በባቡር ጣቢያው ላይ ተመድበው ሲሠሩ የነበሩ የፖሊስ አባላት ባደረጉት ፍተሻ ከነዶላሩ በቁጥጥር አውለውታል ነው የተባለው።

ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና የውጪ ሀገራት ገንዘቦችን በሕገ-ወጥ መንገድ የመመንዘር ወንጀል የኑሮ ውድነት እንዲያሻቅብ ከማድረግ ባሻገር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ይህንን ሕገ-ወጥ ድርጊት ባለመፈፀም እና የሚፈፅሙ አካላትንም ለሕግ አሳልፎ በመስጠት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል።