ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምት ያለው ዓለም ዐቀፍ የግዥ ጨረታ ተሰረዘ

ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምት ያለው ዓለም ዐቀፍ የግዥ ጨረታ መሰረዙን የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በጤና ሚኒስቴር ግዥ ጠያቂነት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለ2014 በጀት ዓመት የወባ መከላከያ አጎበር ግዥ ለመፈጸም ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምት ያለው ዓለም ዐቀፍ የጨረታ የግዥ ሂደት ህግን የተከተለ ባለመሆኑ ጨረታው መሰረዙን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ በቀረበለት ጥቆማ መሰረት የጨረታው አሸናፊ ተደርጎ የተመረጠው ድርጅት የሀገር ውስጥ የወባ መከላከያ አጎበር የማረጋገጫ ፍቃድ የሚሰጡና የሚያድሱ አካላት ኃላፊነት በግልፅ አለመቀመጡን እንደ ምክንያት አድርጎ በመውሰድ ካስቀመጣቸው ሦስት ወኪሎች በአንደኛው ተወካይ ህግን ባልተከተለ መልኩ በተጭበረበረ ሁኔታ ህገ-ወጥ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የወሰደና በጨረታው እንዳይወዳደር የተሰረዘበት መሆኑን አረጋግጧል።

ሆኖም በሌላኛው ተወካይ በተሰጠ የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት በመወዳደር የጨረታው አሸናፊ እንዲሆን መደረጉ፣ የዋናውን ድርጅት ከተጠያቅነት እንደማያድነውና የግዥው ሂደት ጤናማ አለመሆኑን ኮሚሽኑ ከማጣራት ሂደቱ መረዳቱን ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ባካሄደው የአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራና  ባረጋገጣቸው ግኝቶች ላይ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ግዥውን ከሚፈፅመው ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ የጋራ ግንዛቤ መያዙን አስረድቷል፡፡

ይህ ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምት ያለው ዓለም ዐቀፍ ግልፅ ጨረታ ግዥ ለ17 ሚሊየን 809 ሺሕ 388 የወባ መከላከያ አጎበሮች ግዢ ጨረታ የወጣ ሲሆን ሂደቱ ለሙስናና ብልሹ አሠራር የተጋለጠ ስለመሆኑ በማጣራት ግኝቱ የማስተካከያ ምክረ ሀሳቦችን የያዘ ሪፖርት ለጤና ሚኒስቴር እና ከላይ ለተመለከቱት መንግሥታዊ ተቋማት ማሳወቁን አብራርቷል፡፡

ከዚህ በመነሳት የጤና ሚኒስቴር ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ የሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ የጨረታ ሂደቱ በተጭበረበረ ሰነድ መሆኑን ያረጋገጠውን የዓለም ዐቀፍ ጨረታ ማስቀጠል በግዥው ሂደት ላይ የነበረን ስጋት እንዲቀጥል የሚያደርግና ውጤቱ ለሚኒስቴሩ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊፈጠር እንደሚችል በመጥቀስ ሚኒስቴሩ ጨረታውን መሰረዙን አስታውቋል፡፡

ይህንኑ ውሳኔ ተጫራቾች እንዲያውቁት እንዲደረግ ለኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ማሳወቁንም ነው ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡

ኮሚሽኑ ያቀረበው ምክረ ሀሳብ ተቋማት ሙስና እና ብልሹ አሠራርን በራስ ውሳኔ ወደ መከላከል የሚያደርስ በመሆኑ ሚኒስቴሩ ይህንኑ ምክረ ሀሳብ በመቀበል የእርምት እርምጃ መውሰዱ አርያነት ያለው ተግባር ነው፡፡

ዓለም ዐቀፍ የግዥ ጨረታውን በተመለከተ የግዥ ሂደቱ “ህግን የተከተለ አይደለም” የሚል ጥቆማ ለፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ቀርቦ  ከየካቲት 8 እስከ 24 ቀን 2014 ዓ.ም በአስቸኳይ የሙስና መከላከል የማጣራት ሥራ ማከናወኑንም ኮሚሽኑ አውስቷል፡፡