ሐምሌ 23/2013 (ዋልታ) – የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ሠራተኞችና ተማሪዎች ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ አደረጉ፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሁሉም ካምፓሶች ተወካዮች ተገኝተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሠጥተዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የውስጥ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶክተር ታደሰ አክሎግ እንዳሉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠት አንዱና ዋነኛ ተግባሩ ነው፡፡
ይህንን ሥራ አጠናክሮ በመቀጠል ሀገር በችግር ላይ በሆነችበት ወቅትም ድጋፍ ማድረግ በማስፈለጉ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የወር ደመወዛቸውን ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህራን ተወካይ ተመስገን ሲሳይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ሠራተኞች የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል ከደሞዛቸው ባሻገር በሞራል፣ በቁሳቁስ እንዲሁም የሕይወት መስዋእትነትን እስከመክፈል ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዘንዘልማ ካምፓስ ማኔጅንግ ዳይሬክተር ታደሠ መኳንንት የካምፓሱ ሠራተኞች ከከተማ አስተዳደሩ የቀረበለትን የዳቦ ዱቄት ወደ ደረቅ ምግብ በመለወጥ ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪ የእርድ እንስሳትን ለህልውና ዘመቻው አበርክቷል ብለዋል፡፡
በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ደጋለም ባዬ የሆስፒታሉ ማኅበረሰብ በግንባር የተሠለፈው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ደረጃውን የሚመጥን ድጋፍ እና እንክብካቤ ለማድረግ ሆስፒታሉ ራሱን እያዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪ መንግሥት በሚያስተላልፈው ሀገራዊ ጥሪ ግንባር ድረስ በመሄድ በሙያቸው ለማገልገል ሁሉም ቁርጠኛ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ዶክተር ደጋለም ኮሌጁ በጎ ፈቃደኞችን በማሰልጠን በቦታው ላይ ተገኝተው የመጀመሪያ የሕክምና እርዳታ የሚያደርጉ ሰዎችን ለማሰማራት እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት አብርሃም ታደሰ እንደነገረን ተማሪዎች ለህልውና ዘመቻው የአራት ቀን ቁርሳቸውን እና የሁለት ቀን እራት የሥጋ ወጭ በድምሩ አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ደግፈዋል፡፡ በተጨማሪ በሁሉም ካምፓሶች ተማሪዎች ደም እየለገሱ መሆኑ አሚኮ ዘግቧል፡፡